በሰሃራ የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር በሜዲትራንያን ከሚሞቱት ሊልቅ ይችላል

የፊቶ ምንጭ: ጆ ፔኒ/ሬውቶርስ፡፡ ከኒጀር ወደ ሊቢያ የሚጓዙ ስደተኞች፡፡

የተባበሩት መንግስታት እንዳለው፤ የአውሮፓ የባህር ዳርቻዎች ላይ ለመድረስ የሜዲትራንያን ባህርን በሟቋረጥ ላይ ሳሉ ሂወታቸውን ከሚያጡት በላይ በሰሃራ የሚሞቱት የምዕራብ አፍሪካ ስደተኞች ቁጥራቸው በብዙ ሊልቅ እንደሚችል ይገመታል፡፡

የዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት የምዕራብና የመካከለኛው አፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ሪቻርድ ዳንዚገር በጄኔቫ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲናገሩ እንዳሉት፤ በሰሃራ በረሃ የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር በተመለከተ እቅጩን የሚናገር አሃዝ ባይኖራቸውም፤ ቁጥሩ ከፍ ያለ እንደሆነ ግን ገልፀዋል፡፡

“ከዚህ በፊትም እንደገለፅነው፤ ቢያንስ በሜዲትራንያን ባህር ከሚሞቱት እጥፍ ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡ ይህን ለማለት በእውነቱ ማስረጃ የለንም፤ ይህ ግምታችን ነው፡፡ እርግጡን አናውቅም፡፡” ብለዋል ዳንዚገር፡፡

በኒጀር የሚገኙ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ከግዜ ወደ ግዜ ባለስልጣናትን እየፈሩ መምጣታቸውንና ይህም ደግሞ ስደተኞችን በረሃው ላይ ብቻቸውን ጥለዋቸው እንዲጠፉ እየገፋፋቸው እንደሆነ ዳንዚገር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

በኒጀር በኩል የሚደረገው ህገወጥ የስደተኞች ዝውውር አሁን እየቀነሰ የመጣ ሲሆን፤ ይህም ሊሆን የቻለው የሀገሪቱ መንግስት ስደተኞች የሚቆዩባቸው “ደሳሳ” መኖርያዎችን በመዝጋትና ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን በማሰር ህገወጥ የሰው ዝውውር ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን በመውሰዱ ነው፡፡

ዳንዚገር በተጨማሪም በሊቢያ በኩል ለማቋረጥ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቶ የተመለሱ ስደተኞች የገጠሟቸውን አስፈሪ ታሪኮች በተመለከተም ተናግረዋል፡፡ “ሊቢያ ውስጥ መታሰር አትሹም፡፡ ሊቢያ ውስጥ የሚሆነው ነገር ለሰዎች ከሞትም በላይ የሚያስፈራ ነው፡፡” ብለዋል፡፡