በህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች የሚደርስ ብዝበዛ

ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አንድን ስደተኛ ወደ አውሮፓ ድንበሮች ለማድረስ በርካታ ገንዘብ ያስከፍላሉ፡፡ አውሮፓ ለመድረስ በጣም ቀላል ነው እያሉ ስደተኞችን ማታለል የተለመደ ሥራ ነው፡፡ ከዚሁም ሌላ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ከስደተኛው ጋር መጀመርያ ላይ ያደረጉትን ስምምነት የማፍረስ ባህርይ አላቸው፡፡ ድንገት ተጨማሪ ገንዘብ እንድትከፍል ይጠይቁሃል፣ አንተን እንደመያዣ በመጠቀም ከወዳጅ ዘመድ የማስለቀቅያ ብር እንዲላክላቸው ያስገድዳሉ፣ እንዲሁም ደግሞ ከመጠን በላይ በታጨቀና አደገኛ በሆነ ሁኔታ እንድትጓጓዝ ያደርጋሉ፡፡

ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች የሚታወቁበት ሌላው መለያቸው፤ ሰዎችን ለሌሎች ወንበዴዎች መሸጥ፣ ስደተኞችን ጠልፈው በመውሰድ የግዳጅ ሥራ ላይ ማሰማራት፤ ከስደተኞች ቤተሰብ ገንዘብ እንዲላክላቸው ማስገደድ እና በመሳሰሉት ድርጊቶች ነው፡፡ ሊቢያ ውስጥ፤ እራስህን በአንድ እስር ቤት ውስጥ ተቆልፎብህና ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋልጠህ ልታገኘው ትችላለህ፡፡ ሌሎች ስደተኞች ደግሞ ዕዳቸውን ለመከፈል ሲሉ አሊያም ለሚቀጥለው ጉዟቸው ገንዘብ ለማጠራቀም ሲሉ ለባርነት ይዳረጋሉ፡፡ ይኸውም ለሴቶች የሴተኛ አዳሪነት ሥራ፣ ለወንዶች ደግሞ ከባድ አካላዊ ስራን ማሠራት ነው፡፡

ስደተኞች ለህገወጥ አዘዋዋሪዎቻቸው የሚከፈል ገንዘብ ካጡ የሰውነታቸውን አካላት በልተው ለሚወስዱ የተደራጁ የወንጀለኞች ቡድኖች ተላልፈው እንደሚሸጡ የሚገልፁ ሪፖርቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በቅርቡ አንድ ኤርትራዊ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ፤ የተጠየቁትን መክፈል ያልቻሉ ስደተኞች የሰውነት አካላቸውን በልቶ መውሰድ ለሚፈልግ አንድ የግብፅ የወንጀል ቡድን መሸጣቸውን መስክሯል፡፡

በሊቢያ የሚገኙ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ትርፋቸውን ለማካበት ለጥቂት ሰዎች በተሠራች ጀልባ ውስጥ በርካታ ስደተኞችን አጭቀው ይጭናሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ጀልባዎቹ ሜዲትራንያንን በደህና ማቋረጥ አይሆንላቸውም፡፡ በ 2016 ከ 5,000 ሺ በላይ ስድተኞች የሞቱ ሲሆን – አብዛኞቹም ከሊቢያ ወደ ኢጣሊያ ሲሄዱ ሜዲትራንያን ላይ የሞቱ ናቸው፡፡

ያለፈ ገፅ
ለሌላ ያካፍሉ