አደገኛው የሊቢያ መንገድ

ሊቢያ አውሮፓ ለመድረስ የሚፈልጉ ሕገወጥ ስደተኞች፤ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ጨምሮ፤ እንደ ዋና መሸጋገርያቸው የሚጠቀሙባት እምብርት ናት፡፡ ሙዓመር ጋዳፊ በ 2011 (እ.ኤ.አ) ከሥልጣን ከተወገዱ ጀምሮ፣ ማንም ኃይል ሙሉ ለሙሉ ሥልጣን መቆጣጠር ባልቻለበት ሁኔታ አገሪቷ ወደ ኃይለኛ ትርምስ ወድቃለች፡፡ በዚሁ ምክንያትም ሊቢያ ያልተረጋጋች፣ አደገኛና በግልፅ በሚታይ መልኩ ሕግ አልባ አገር ሆና ቀጥላለች፡፡ በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች ለህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ መረቦች እጅግ የተጋለጡ ከመሆናቸውም በላይ ተስፋ የቆረጡ በመሆናቸው በወንበዴዎች ይበዘበዛሉ፡፡

በሊቢያ የነበሩ ስደተኞች ለእጅግ ከባድ ጥቃት፣ የገንዘብ ቅሚያ፣ ላልተወሰነ ግዜ መታሰርና ለባርነት ሥራ እንደተዳረጉ ይናገራሉ፡፡ ብዙ ስደተኞች፤ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ጭምር፤ ሌላ ስደተኛ በሊቢያ ሲገደል ማየታቸውን እንዲሁም ደግሞ እራሳቸው ወይም ሌሎች ለአካላዊ ጥቃት ተጋልጠው እንደነበር ይመሰክራሉ፡፡

በርካታ የኢትዮጵያና ኤርትራ ስደተኞች በሊቢያ እስር ቤቶች ለብዙ ጊዜ ይማቅቃሉ፡፡ በእስር ቤት እያሉም በእስረኛ ስደተኞችና በዘበኞች ጭካኔ የተሞላበት ተደጋጋሚ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ የግዳጅ ሥራ መደበኛ ከመሆኑም በላይ ለእስረኞቹ የሚሰጠው ምግብና ሕክምና እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ረዳትነት ከሊቢያ ጠረፍ የሚነሱትን ስደተኞች ከጉዞአቸው ማስተጓጎል ይችሉ ዘንድ የአውሮፓ ኅብረት ለሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ሥልጠና በመስጠት ላይ ነው፡፡ በሊቢያ የባህር ግዛት ላይ እንዳሉ በሊቢያ የጠረፍ ጠባቂዎች የተያዙ ስደተኞች ተመልሰው ወደ ሊቢያ ይላካሉ፡፡ አገሪቷ የነፍስ አድን ስራ የሚያከናውኑ መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ወደ ባህር ግዛቷ እንዳይጠጉ አግዳለች፤ ይህ ማለት ከሊቢያ አቅራቢያ ሲከናወኑ የነበሩ ስደተኞችን የመታደግ ስራዎች ቆመዋል፡፡

ያለፈ ገፅ
ለሌላ ያካፍሉ