የአውሮፓ የስደት ፖሊሲዎች
ብዙ ጊዜ ሕይወት በአውሮፓ፣ ስደተኞች እንደሚያስቡት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፤ ብዙ ስደተኞች አውሮፓ ከደረሱ በኋላ የት መኖር እንደሚፈልጉ መወሰን እንደሚችሉና ሥራም ቢሆን በቀላሉ እንደሚያገኙ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ሁኔታው እንደዛው አይደለም፡፡
ጥገኝነት ለማግኘት ማመልከት
በአውሮፓ ህብረት ሕግ መሠረት፤ አንድ ስደተኛ መጀመርያ በገባበት ሀገር ነው የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ ያለበት፡፡ ይህ ማለት መጀመርያ የገባህበት አገር ኢጣሊያ ወይም ግሪክ ከሆነ፤ የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ ያለብህ በእነዚህ ሀገራት ነው፡፡ መኖር የምትፈልግበትን የአውሮፓ አገር መምረጥ አትችልም፡፡
ለጥገኝነት ስታመለክት አብዛኛውን ጊዜ በስደተኞች መቀበያ ማእከል ውስጥ እንድትኖር ይደረጋል እንጂ መቆየት የምትፈልግበትን ቦታ አንተው መወሰን አትችልም፡፡ እነዚህ የማቆያ ማእከላት ለምግብና ለአንዳንድ መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚሆን በየወሩ በጣም ትንሽ ገንዘብ የሚሰጡ ቢሆንም፤ ይህ ግን ምንም እንድትቆጥብ የሚያስችልህ አይደለም፡፡
ሥራ መቀጠር
በአብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች፤ የጥገኝነት ማመልከቻህ ገና በሂደት ላይ ባለበት ወቅት መሥራት አይፈቀድልህም፡፡ ብዙ ጊዜ ሊሚወስድ የሚችለው የጥገኝነት ጥያቄህ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው ሥራ ማፈላለግ የምትችለው፡፡ ያኔም ቢሆን የሚፈለገው የሙያ ብቃት፣ ልምድ፣ የትምህርት ደረጃና የቋንቋ ክህሎት ከሌለህ ሥራ ማግኘት ከባድ ሊሆንብህ ይችላል፡፡ በአውሮፓ የሚከፈል የሥራ ክፍያ በኤርትራ ወይም በኢትዮጵያ ከሚከፈለው ክፍያ ላቅ ያለ ቢሆንም፤ የኑሮ ሁኔታ ግን በጣም ውድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስደተኞች የአውሮፓ የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ቸል ቢሉትም፤ ምግብ፣ ቤት፣ ትራንስፖርትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እጅግ በጣም ውድ ናቸው፡፡
ብቸኝነት
ብዙ ስደተኞች አውሮፓ እንደደረሱ ስለ ብቸኝነታቸው ያማርራሉ፤ ሀገር ቤት ጥለዋቸው የመጡትን ጓደኞቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን መናፈቃቸውን ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በአውሮፓ ሕይወት ለመላመድና ከሕብረተሰቡ ጋር ለመዋሃሀድ የቋንቋና የባህል ገደቦች ያጋጥሟቸዋል፡፡