ኤርትራዉያን ስደተኞች ወደ አዉሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ አስከፊ ጥቃት ይደርስባቸዋል

TMP – 15/03/2017

በድንበር የለሽ ሃኪሞች (MSF) የወጣ ሪፖርት እንሚያመለክተዉ ወደ አዉሮፓ ለመድረስ የሚሰደዱ ኤርትራዉያን በሚጓዙባቸዉ ቦታዎች አስከፊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፡፡

ይህ ‹‹ኤርትራዉያን ደህንነትን በመሻት ወደ አዉሮፓ የሚያደርጉት የሞት ጉዞ ›› በሚል ድርጅቱ በሚገኝባቸዉ ፕሮጀክቶች ፣ሊቢያ ኢትዮጵያና በሚድትራንያን የነብስ አድን ጀልባዎች ላይ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ስደተኞች ባደረገዉ ቃለምልልስና ከ106 ኤርትራዉያን ስደተኞች ባገኘዉ የአይን ምስክርነትና ተጨባጭ መረጃ መሰረት በማድረግ ባወጣዉ ሪፖርት ኤርትራዉያን በየቀኑ በከባድ የአካላዊ ቁስል ጠባሳ እና የሰነአእምሮ ጭንቀት ዉስጥ እንደሚገኙ ከሚሰጡት መረጃ የሚታይ የተለመደ ክስተት ነዉ ብሏል፡፡

ለኤርትራዉያን ከአገራቸዉ ያለ መዉጫ ቪዛ መዉጣት ህገወጥነት ነዉ ያለዉ መረጃዉ የመዉጫ ወረቀቱን ማግኘትም እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነዉ ተብሏል፡፡ ይህን ጥሰዉ ከሃገራቸዉ አምልጠዉ የሚሰደዱት ኤርትራዉያን ለረጅም ጊዜ በኢትዮጰያና ሱዳን የመጠለያ ካምፖች የመቆየት ፈተና እንዲሁም በሊቢያ ለተለያዩ አካላዊና ስነአእምራዊ ችግር፣ የጾታ ጥቃት ፣ እስርና በ2016 የ4500 ሰዎች ህይወትን ለቀጠፈዉ ወደ አዉሮፓ የሚያደርሰዉ አደገኛ የሚድትራንያን ባህር ጉዞ ይጋለጣሉ ብለዋል፡፡

በድንበር የለሽ የሃኪሞች ድርጅት (MSF) የተጠየቁት ሁሉም ኤርትራዉያን ከኤርትራ ወደ አዉሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ በተለያዩ ቦታዎች ወይ በራሳቸዉ ላይ የተለያዩ አስከፊ ጥቃቶች የተፈጸመባቸዉ ናቸዉ ወይም ደግሞ በሌሎች ኤርትራዉያን ሲፈጸም በአይናቸዉ ያዩ ናቸዉ ብሏል፡፡ ከኤርትራ ከሚሰደዱት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሚደርስባቸዉ አስከፊ ጥቃት እንዲሚሞቱም ገልል፡፡

የ 22 ዓመቷ እርጉዝ የነበረች ኤርትራዊ ሴት በጉዞዉ አስከፊነትና አስጨናቂነት እንዴት እርግዝናዋ እንዳስወረዳት ስትናገር ‹‹ ወደ አዉሮፓ ለመጓዝ ወደ ባህር ዳርቻዉ ተወሰድን ፖሊሶች እንድንቆም አደረጉን ፣ ጥይትም ተኮሱብን፣ በፍርሃትና በጭንቀት ልጄን አጣሁት፣ የ6 ወር እርጉዝም ነበርኩኝ ›› ብላለች

በሊቢያ ባለስልጣናት በእስር ቤት ዉስጥ የሚገኙ ስደተኞች ለአካለዊ ክብደታቸዉ ከሚያስፈልጋቸዉ ዕለታዊ ምግብ ከማግሽ በታች እንደሚያገኙ የገለጸዉ ሪፖርቱ የአጥንት፣ የመተንፈሻ ጉሮሮ በሽታ ወረርሽና ከንጽህና ጉድለትና መተፋፈን የተነሳ ለሚከሰት አደገኛ የተቀማጥ በሽታም በእርስ ቤት ቆይታቸዉ የተለመዱ ችግሮች ናቸዉ ብሏል፡፡ የጭንቅላት መጎንዳት የብሽሽት ማበጥና የአንገት መሰበር እንዲሁም ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የቁስል ጠባሳ በእስር ቤት ዉስጥ በሚደርስባቸዉ ተደጋጋሚ ድብድባ ምክንያት እንደተጋለጡም ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

በድንበር የለሽ የሃኪሞች ድርጅት (MSF) የተጠየቁት ኤርትራዉያን ሴቶች ሁሉ ለጾታ ጥቃት አስገድዶ መደፈር በብዙ ወንጀለኞች እና በቀጥታ በራሳቸዉ የተፈጸመባቸዉ ወይም ደግሞ በሌሎች እህቶቻቸዉ ሲፈጸም ያዩ እንደሆኑም ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ከጠየቁት አንዱ ‹‹ ጾታዊ ጥቃት በሴቶች እና እህቶቻችን ላይ ሲፈጸም በአይን ማየት በጣም አሳዛኝ ነበር እንዲያቆሙ ብትነግራቸዉም ይገድሉሃል ወይም እንድትሞት በርሃ ዉስጥ ይጡልሃል›› ሲል ሌላዋ የ20 ዓመት እናት ደግም  ‹‹ከዚህ አደገኛዉ የሞት ጉዞ በማምለጤ ማንም እንዳይመርጠዉ እመክራለሁ፡-ይህ የሞት ጉዞ ለክፉ ጠላቴ እንኳን አልመኝም፣ ዋጋ ቢስነት እንዲሰማህ ፣እንድትንበረከክና ስብእናህ እንዲወርድ የሚያደርግ ነዉ ›› ብላለች፡፡