26 ስደተኞችን ጭና ሲትጓዝ የነበረች የህገወጥ አዘዋዋሪዎች መኪና የመገልበጥ አደጋ ደረሰባት

የተለያዩ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ሲጓዙ የነበሩ 26 ስደተኞች ጭና ስትጓዝ የነበረች ተሸከርካሪ በሰሜናዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሑመራ ከተማ የመገልበጥ አደጋ ደርሶባት አንድ ሰዉ ሲሞት የተወሰኑት የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡

መኪናዋ 18 ወንዶች እና 8 ሴቶች የጫነች ሲሆን እነዚህም ህፃፅ ከተባለ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከሚገኝ የስደተኞች ካምፕ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ተደልለው የወጡ ናቸዉ፡፡

አደጋው የደረሰው መጋቢት 18 ከሌሊቱ 1፡30 ሽመልባ በመባል ከሚታወቀውና ከተቋቋመ ረጅም ዓመት ካስቆጠረው ኤርትራውያን ስደተኞች ከሚገኙበት የመጠለያ ጣብያ ሦስት ኪሎ ሜትር እንደተጓዘች ነው፡፡

አንድ ስደተኛ አደጋው በደረሰ ወዲያውኑ ሲሞት 11 ወንዶችና አንዲት ሴት በከባድ ቆስለው ወደ ሸራሮ፣ ሽሬና አይደር ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ የቀሩት 14 ስደተኞች ደግሞ ወደ ሕፃፅ የመጠለያ ካምፕ ተመልሰዋል፡፡

የአደጋዉ መነሻ እስካሁን በሚመለከተው የመንግስት አካል ይፋ ባይሆንም ህገወጥ ዘአዋዋሪው በርካታ አልኮሎችን እየጠጣ ሲያሽከረክር እንደነበረ ተጓዦቹ ተናግረዋል፡፡ ህገወጥ አዘዋዋሪው አደጋው በደረሰ ቅጽበት ከአካባቢዉ የተሰወረ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ማንነቱ እንዳልታወቀም ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ባለስልጣናት በመጠልያ ጣብያው ስደተኞችን በመደለል ለህገወጥ አዘዋዋሪው አስረክበዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ማሰራቸውም ተገልጿል፡፡

ህገወጥ አዘዋዋሪዎች በትግራይ ክልል በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ መኖር እጅግ የተሰላቹና ተስፋ የቆረጡ ስደተኞችን ዒላማ በማድረግ እየሰሩ ሲሆን ወደ ሱዳን ሊቢያና ካዛም ወደ አውሮፓ እናሻግራችኃለን በሚል እንደሚደልሉዋቸው መረጃው ጠቁሟል፡፡

ባለፈው ወር 78 ኤርትራውያን ስደተኞች የጫነ ተሸከርካሪ ከትግራይ ክልል ተነስቶ ሲጓዝ ሱዳን ውስጥ ባጋጠመው ዘግናኝ አደጋ 51  ስደተኞች የሞቱ ሲሆን በአደጋው የቆሰሉ 27 ስደተኞችን ጭኖ ወደ ሆስፒታል ሲጓዝ የነበረ መኪናም በደረሰበት አደጋ 25 ስደተኞች መሞታቸዉ የሚታወቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ህገወጥ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል አዲስ ህግ አውጥቶ እየሰራ ሲሆን በዚህ ህገወጥ ስራ ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉት ደግሞ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት እንደሚወሰንባቸው ተገልል፡፡ አዲሱ ህግ እንደወጣ ብዙ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ረጅም የእስራት ዘመን ተፈርዶባቸዋል፡፡