የኢጣሊያ ፖሊስ ሜዲትራንያን ላይ ሞተው የተገኙ ሴቶች ግድያ ተፈፅሞባቸው እንደሆነ እየመረመረ ነው
የፎቶ ምንጭ: ANSA. የነፍስ አድን ሰራተኞች በኢጣሊያ የሳሌርኖ ወደብ ‘ካንታብሪያ’ በምባለው የስፔን መርከብ ሬሳዎችን ሲያነሱ፡፡
ሜዲትራንያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ የሞቱ የ 26 ታዳጊ ናይጄርያውያን ሴቶች ሬሳ በፈረንጆቹ ህዳር 5 ተገኝቷል በማለት የኢጣሊያ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የሴቶቹ ሬሳ ባለቤትነቷ የስፔን በሆነችውና ዘመቻ ሶፍያ ተብሎ በሚጠራው ሜዲትራያን ላይ ፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሚደረገው ዘመቻ ላይ ተሳታፊ በሆነችው ካንታብሪያ የተሰኘችው መርከብ ወደ ደቡባዊቷ የጣሊያን ወደብ ሳሌርኖ ተወስዷል፡፡ የካንታብሪያ መርከብ ሰራተኞች 23 ሬሳ ከአንድ የተሰባበረ ጀልባ ላይ ያገኙ ሲሆን ሌሎች ሶስት ደግሞ ከሌላ ላይ አግኝተዋል፡፡ ስድሳ ሰዎች መታደግ የተቻለ ሲሆን 53 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ (UNHCR) ቃልአቀባይ የሆኑት ማርኮ ሮቱኖ እንዳሉት ሬሶቹ ወደ ሳሌርኖ ሲመጡ የስራ ባልደረቦቻቸው በቦታው ላይ ነበሩ፡፡ “በጣም ከባድ ሁኔታ ነው“ ነበር ያሉት፡፡ “አንዲት ከናይጄርያ የመጣች ሴት ሁሉንም ሶስት ልጆቿን አጥታለች፡፡“
የኢጣሊያ አቃብያነ ህግ ወድያውኑ ምርመራ ጀምረዋል፤ እነዚህ ከ 14 እስከ 18 ዓመት እድሜ እንዳላቸው የተገመቱት ሴቶች ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ተገድለው ለሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ ነው ምርመራው የተጀመረው፡፡
ሮቱና ጨምረው እንደገለፁት፤ 90 ከመቶ የሚሆኑት ስደተኛ ሴቶች ጥቃት እንደደረሰባቸው የሚያመላክቱ ጠባሳዎችን እና ሌሎች ምልክቶችን ይዘው ነው የሚደርሱት፡፡ “ጥቃት ያልደረሰባት ሴት ማግኘት በጣም ከባድ ነው፤ አንዳንዴ ነው የሚያጋጥመው፤ ምናልባት ከባላቸው ጋር የሚጓዙ ከሆነ ብቻ፡፡ ነገር ግን ሴቶች ልጆቻቸውን ይዘው ለብቻቸው ሲጓዙም ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡“
የኢጣሊያ መርማሪዎቹ ፆታዊ ጥቃት መፈፀሙን የሚያረጋግጥ እስካሁን ድረስ የተገኘ ማስረጃ እንደሌለ የተናገሩ ቢሆንም፤ የተባበሩት መንግስታት እንደሚለው ግን ኢጣሊያ ከሚደርሱት ናይጄርያውያን ሴቶች 80 ከመቶ የሚሆኑት ታዳጊ ሴቶች መጀመርያውኑም ለወሲብ ስራ ደላሎች ቁጥጥር ስር የወደቁ አልያም ተሎ በወጥመዳቸው ይወድቃሉ፡፡
ከጀልባዎቹ አንዷን እየመሩ እንደነበር የታመነባቸው ሁለት ሰዎች በኢጣሊያ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ክስም ተመስርቶባቸዋል፡፡ ከአደጋው በተረፉት ሰዎች ተለይተው የታወቁት እነዚህ ሰዎች አል ማብሩክ ዊሳም ሃራር የተባለ ከሊቢያ እና መሓመድ አሊ አል ቦውዚድ የተባለው ሰው ደግሞ ከግብፅ ናቸው፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ