አልጀርያ ስደተኞችን በግድ እያባረረችና በረሃው ላይ እየጣለች ነው
የፎቶ ምንጭ: IOM/አማንዳ ኔሮ 2016/ ከአልጀርያ የተመለሱ ናይጄርያውያን ስደተኞች በኒጄር አጋዴዝ በሚገኝ የ IOM የመሸጋገርያ ማዕከል ላይ፡፡
አልጀርያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት የመጡባትን ስደተኞች አስገድዳ ከሀገሯ በማስወጣት ከኒጀር ጋረ በምትዋሰንበት ድንበሯ አካባቢ ባለው በረሃ ላይ ካለ ምንም ዕርዳታ እየጣለቻቸው ነው ሲሉ የፈረንሳይ አለምዓቀፍ ራዲዮ (RFI) እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልፀዋል፡፡
ስደተኞቹ በሌሊት ይከበቡና በዋና ከተማዋ አልጀርስ አካባቢ ወደሚገኙ የእስር ማዕከላት ይወረወራሉ፤ በኋላም በጦር መኪና ተጭነው ይወሰዱና በአልጀርያዋ ታማንራሰት እና በኒጀርዋ አርሊት መካከል በሚገኘው በረሃ ላይ እንዲጣሉ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ስደተኞቹ የሚታደጋቸው እስኪያገኙ ድረስ በእግር ለአራት ሰዓታት እና ምናልባትም ለቀናት አስከፊ በሆነ ሁኔታ ይጓዛሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደት ጉዳዮች ኤጄንሲ የሆነው IOM፤ በአልጀርያ ባለስልጣናት በናይጄርያ በረሃዎች ላይ እንዲጣሉ የተደረጉ እስከ 1000 የሚደርሱ ስደተኞች መታደጉን አረጋግጧል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው የጥቅምት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርቱ እንዳመለከተው፤ አዲሱ የእስር ሁኔታ የጀመረው በፈረንጆቹ መስከረም 22 ላይ የአልጄርያ ፖሊስና ዣንዳራም ታጣቂ ሃይሎች በአልጀርስ ከተማና ዙርያዋ የሚገኙ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት የመጡ ስደተኞችን በማንአለብኝነት ማሰር እንደጀመሩ ነው፡፡ ይህን ያደረጉት ባለስልጣናት ስደተኞቹ ሀገሪቱ ውስጥ የመቆየት መብት ይኑራቸው አይኑራቸው አላረጋገጡም፤ ፓስፖርትም ይሁን ሌላ ሰነድ አልተመለከቱም ብሏል ሪፖርቱ፡፡ ከታሰሩትና ከተባረሩት ስደተኞች መካከል አንዳንዶቹ ያልተመዘገቡ ስደተኞች ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ህጋዊ ቪዛ የነበራቸው ናቸው፡፡
“በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የቆዳቸው ቀለም ወይም ከዚህ ሀገር የመጡ ናቸው በሚል እሳቤ ከበባ ማድረግና በግድ ከሀገር አውጥቶ ማባረር ትክክል የሚሆንበት ገለፃ ሊኖር አይችልም – ይህ በግልፅ የሚታይ ዘር መሰረት አድርጎ የመለየት አሰራር ነው፡፡” ብለዋል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰሜን አፍሪካ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ሄባ ሞራየፍ፡፡
በአሁኑ የጥር እና የካቲት ወራት ውስጥ ባሉ ቀናት፤ ከሁለት እስከ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ከማዕከላዊና ከምዕራብ አፍሪካ የመጡ ስደተኞች በግድ ከአልጀርያ ግዛት እንደተባረሩ ተነግሯል፡፡ ከተባበሩት መካከል ለረጅም ዓመታት አልጀርያ ውስጥ የኖሩና የሰሩ፣ ነፍሰፁር ሴቶች፣ ጨቅላ ህፃናት እና ወላጅ አልባ ልጆች ይገኙባቸዋል፡፡
ኒጀር ዜጎቿ አልጀርያ ውስጥ የሚፈፀምባቸውን ኢሰብአዊ አያያዝ በተመለከተ ያላትን ተቃውሞ በተደጋጋሚ የገለፀች ሲሆን፤ ጊኒ፣ ጋቦን እና ኒጀር ውስጥ የሚገኙ ሲቪክ ማህበራት ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ እንዲይዘው ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡
በ RFI ዘገባ መሰረት፤ አልጀርያ በቅርቡ ተጨማሪ 3000 ስደተኞችን ከሀገሯ ለማባረር እየተዘጋጀች ነው፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ