ሊቢያ የሚገኙ 200 ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች የእስር ማዘዣ ተቆረጠባቸው

ወደ አውሮፓ ሰዎችን በህገወጥ መንገድ በማሸጋገር እና ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 200 ሊቢያውያን እና ሎሎች የውጭ ዜጎች የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል፡፡
“በተደራጀ ህገወጥ ስደተኞችን የማሸጋገር እና የማዘዋወር ወንጀል፤ እንዲሁም ስደተኞችን በማሰቃየት፣ በመግደል እና በመድፈር ተሳታፊ የሆኑ 205 ሰዎችን ለማሰር የትእዛዝ ወረቀት ይዘናል” ብለዋል የጠቅላይ አቃቤ ህግ የምርመራ ፅህፈት ቤቱ ዳይሬክተር የሆኑት ሰዲቅ አል-ሱር በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡
አል-ሱር እንዳሉት፤ የሊቢያ የፀጥታ ሃይሎች፣ የእስር ማእከላት ሃላፊዎች፣ እንዲሁም በሊቢያ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የኤምባሲ ሓላፊዎች በዚህ ህገወጥ የሰው ዝውውር መረብ ውስጥ እጃቸው አለበት ተብሎ ተጠርጥረዋል፡፡
በህገወጥ የሰው ዝውውር፣ ሰዎችን በመሸጥ ወይም በማሰቃየት ተግባር፤ ስደተኞች በህገወጥ መንገድ እንዲገቡ ወይም ዋስትናቸው ባልተጠበቁ ጀልባዎች ላይ እንዲሳፈሩ በማድረግ ተግባራት ላይ መሳተፋቸው የተረጋገጠ ሰዎች እስከ ዕድሜ ልክ እስራት የሚደርስ ከባድ ቅጣት የጠብቃቸዋል፡፡
በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበና በዚሁ ዓመት መጀመርያ ይፋ የተደረገ አንድ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ፤ የሊቢያ የፀጥታ ሃይሎች ከህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ሲል ይከሳል፡፡ ”የሌላ ትልቅ ፖለቲካዊና-ወታደራዊ ጥምረት አካል የሆኑ ታጣቂ ቡድኖች፤ ህገወጥ በሆኑ የዝውውር ተግባራት ላይ የተሰማሩ ናቸው፤ በተለይም በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ” ሲሉ ባለሙያዎቹ ያስቀምጣሉ፡፡
መቀመጫውን ትሪፖሊ ላይ ካደረገው መንግስት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተባብሮ የሚሰራውና፣ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን መመርመር እንዲሁም ስደተኞች ማሰርን ጨምሮ የፖሊስ እንዲሁም የፀጥታ ተግባራትን እንዲያከናውን ስልጣን የተሰጠው SDF በመባል የሚታወቀው ልዩ የመከላከያ ሃይል ስደተኞችን በብር ለህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ አሳልፎ እንደሚሰጥ በባለሙያዎቹ ሪፖርት ላይ ተገልጿል፡፡
ይህ በተባበሩት መንግስታት ሪፖርቱ ላይ የተገለፀው ጥርጣሬ በጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ መርማሪ የተረጋገጠ ሲሆን፤ በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አካላት ለገንዘብ ሲሉ ስደተኞችን በመልቀቅ አልያም ስደተኞችን ለህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በመሸጥ ወንጀሎች መከሰሳቸውን መርማሪው ተናግረዋል፡፡