ሀንጋሪ ላይ የቀረበው ረቂቅ ህግ ስደተኞችን የሚረዱ የእርዳታ ድርጅቶችን ስራ ለመገደብ አቅዷል
የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን
የሀንጋሪ መንግስት ወደሀገሪቱ የሚደረግ ስደትን የሚደግፉ የዕርዳታ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ግብር ለመጣል እና ሌሎች በርካታ ገደቦችን ያደርግ ዘንድ ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ስልጣን የሚሰጥ ረቂቅ ህግ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አቅርቧል፡፡ ይህ ሂደት የተከናወነው በፈረንጆቹ የካቲት 8 ለመካሄድ ዕቅድ ከተያዘለት ብሄራዊ የህግ አርቃቂ ምክርቤቱ ምርጫ ቀደም ብሎ ነው፡፡
ረቂቁ እንደሚለው “የሶስተኛ ሀገር ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቁ ሀገራትን ተሻግረው ዓለምአቀፍ ጥበቃን ያገኙ ዘንድ ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ ወይም ሀገሪቱ ውስጥ እንዲቆዩ የሚደግፍ፣ የሚያደራጅ ወይም የሚያበረታታ” የእርዳታ ድርጅት ስደትን ከሚያበረታቱት ወገን ይመደባሉ፡፡ የተሟጋችነት ስራ የሚሰሩ፣ በጎ ፈቃደኞችን የሚያሰማሩ እና መረጃ ሰጪ ፅሁፎችን የሚያሰረጩ ድርጅቶችም በዚሁ ምድብ ተካተዋል፡፡
ቀደም ብሎ በተጠቀሰው ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን ማከናወን የሚችሉት በሀንጋሪ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እውቅና ከተሰጣቸው ብቻ ነው፤ ሚኒስትሩ “ሀገራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል” ሁኔታ ካየ ፍቃዱን መከልከል ይችላል፡፡
ስደትን ከሚደግፉ የውጭ ሀገር የዕርዳታ ድርጅቶች የሚገኝ ልገሳ ላይ 25 በመቶ ታክስ መጫን፤ እንዲሁም ደግሞ ስደትን የሚደግፉና ከሀንጋሪ ብሄራዊ የደህንነት ጥቅሞች ተቃራኒ የሚሆኑ እንቅስቃሴዎችን የሚያከናውኑ አቀንቃኞች እና ተሟጋቾች ላይም ገደቢ ትዕዛዞችን ማስተላለፍ የረቂቅ ህጉ አንኳር ነጥቦች ናቸው፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች የመሳሰሉ ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጓች ቡድኖች ሂደቱ ስራቸውን እና የሲቪል ማህበራት መብቶችን በቀጥታ የሚጥስ ነው ብለውታል፡፡
“ስደትን የሚደግፉ የዕርዳታ ድርጅቶችን የሚቀጣው አዲሱ ረቂቅ ህግ እጅጉን የሚረብሽ እና በስቪል ማህበራት ላይ የተቃጣ መሰረት አልባ ጥቃት ነው” ብለዋል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ጋውሪ ቫን ጉሊክ በመግለጫቸው ላይ፡፡
“በእውነቱ ከሆነ፤ እነዚህ ረቂቅ ህጎች ከሀገር ደህንነት ጋር እና ድንበር ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እርዳታ የሚያደርጉትን እና ደምፃቸውን ለማሰማት የደፈሩትን አካላት ለማፈን የተደረገ ነው”
“እነዚህ ስደተኞችን በሚደግፉ ሰዎች ላይ የተቃጡት ረቂቅ ህጎች፤ ሀንጋሪ ውስጥ ሰዎች መብቶቻቸውን እንዲያስጠብቁ የሚረዱ ተቋማትን ዝም ለማሰኘት የታሰቡ ናቸው” ያሉት ደግሞ የሂውማን ራይትስ ዎች የአውሮፓ እና ማዕከላዊ ኤስያ ዳይሬክተር የሆኑት ቤንጃሚን ዋርድ፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ