የአውሮፓ ህብረት ህገወጥ አዘዋዋሪዎች የሚያገኙት ቁሳቁስ ለመግታት አቅዷል

ሊቢያ የሚገኙ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ለተሰማሩበት የሰው ንግድ የሚጠቀሙባቸው የፕላስቲክ ጀልባዎች ሞተሮች የመሳሰሉ ቁሳቅሶች በእጃቸው እንዳይገቡ ለመከላከል የሚያስችል እቅድ አውሮፓ ህብረት አውጥቷል፡፡

ይህ የአውሮፓ ህብረት ውጥን እነዚህ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች በአደገኛው የባህር ጉዞ ስደተኞችን ከሊቢያ ወደ አውሮፓ በማሻገር የሚያገኙት ትርፍ ለማቆምና በዚህ ህገወጥ ጉዞ የሚሞቱ የብዙ ሺህ ስደተኞች ህይወት ለመታደግ ነው፡፡

ይህ በማልታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የቀረበው እቅድ ለዚህ አደገኛ ጉዛ የሚያገለግል ቁሳቁስ በማቋረጥ እንደ አንድ የመፍትሄ አማራጭ ተወስዷል፡፡

“እንዚህ ቁሳቁሶች በቀላሉ ከአውሮፓ ሊቢያ ውስጥ ለሚገኙ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ይደርሳሉ፣ ስለዚህ ይህን የምንቆጣጠርበት ዘዴ ማበጀት እንዳለብን ነው ለወዳጆቼ ሃሳብ የማቀርብላቸው፡” ብለዋል የማልታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆርጅ ቬላ፡፡

የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት ወደ ሊቢያ የሚላኩ ቁሳቁሶች በህገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ እንደሚገቡ አሳማኝ ምክንያት ካገኙ ለማቆም የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ህብረት አባለ ሃገራት ወደ ሊቢያ የሚላኩ የባህር ትራንስፖርት ቁሳቅሶች ማቆም አልቻሉም፡፡

“ለዚህ አዲስ አቅድ የሚያግዙ ብዙ ሃሳቦች እየመጡ ነው፣ የኛ እቅድ ህጋዊ እውቅና ያለው የንግድ ልውውጥ ለአሉታዊ ተግባር አለመዋሉን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ አዲስ እቅድ ነው የአውሮፓ ህብረት አባለ ሃገራት ይህ ወደ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች የሚደርሰው የቁሳቁስ አቅርቦት ለማቆም ተጨማሪ የአስተዳደር ሸክም ቢፈጥርባቸው እንደሚስማሙ ተስፋ አለኝ፡” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቬላ፡፡

ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የተገኘው ምላሽ እስከ አሁን አበረታች ሲሆን በቅርብ ጊዜ የመጨረሻ ውሳኔአቸው ይጠበቃል፡፡