ኢጣሊያ ህገወጥ የሰው ዝውውር ለመግታት የሚያችሉ ጀልባዎች ለሊቢያ ሰጠች
ኢጣልያ ለሊቢያ የባህር ክልል ጥበቃ በሚድትራንያን ባህር የሚደረገውን ህገወጥ የሰው ዝውውርን ለመግታትና ስደተኞችን ከአደጋ በማዳን ወደ ሊቢያ ለመመለስ እንዲቻል 10 ጀልባዎችን ለመስጠት በገባቸው ቃል መሠረት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ጀልባዎች ሰጠች፡፡ ይህም ኢጣልያ ሚድትራንያን ባህር አቋርጠው ወደ ባህር ክልልዋ የሚገቡ ህገወጥ ስደተኞችን ለመከላከል ያቀደችው ስትራቴጂ አካል ነው፡፡
የሞተር ጀልባዎቹ ርክክብ የተፈጸመው ሚያዚያ 24 ጋዬታ በተባለ የጣልያን ቦታ 20 የሊቢያ የባህር ክልል ጠባቂዎች ስልጠናቸው አጠናቀው በተመረቁበት ወቅት ነው፡፡
የኢጣልያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ቀሪዎቹ ጀልባዎች ኢጣልያ በሰኔ ወር ላይ እንደምታስረክብ ገልፀው የሊቢያ የባህር ክልል ጥበቃ በሰሜን አፍሪካ ያለውን ህገወጥ የሰው ዝውውር ለመቆጣጠር በጣም አስፈላጊ ተቋም ነው ብለዋል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች ግን ህገወጥ ስደተኞቹ ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ ማድረግ ለተጨማሪ አደገኛ ድብደባና ጾታዊ ጥቃት እንዲጋለጡ ማድረግ ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የሊቢያ አምባሳደር አህመድ አልሳፋር በበኩላቸው በሊቢያ እስር ቤቶች የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳለ አምነዋል ‹‹በእስር ቤቶች የሰብአዊ መብት ጥሰት አለ፣ ለወደፊትም ሊኖር ይችላል፣ በዚህ ጉዳይም እንሰራለን፤ ይህን ለመቆጣጠር እና የግንዛቤ ስራ ለመስራት ከሌሎች ሃገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንተባበራለን ብለዋል፡፡ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በሊቢያ ያለው ክፍተት ተጠቅመው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በአነስተኛ ጀልባዎች እየጫኑ ወደ ጣልያን የባህር ዳርቻዎች ማሻገራቸው ቀጥለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት እና ጣልያን በሊቢያ የመጠለያ ካምፕ ለማቋቋምና ህገወጥ ስደተኞችን ለማስፈር እያቀዱ ሲሆን ወደ አውሮፓ የጥገኝነት ጥያቄ የሚጠይቁና ተቀባይነት ያላቸውም ጉዳያቸው በዚያ ካምፕ ሆነው ይፈጽማሉ፡፡
በመጋቢት ወር የአካባቢው ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት የኢጣልያው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ በሊቢያ ስለሚቋቋመው የስደተኞች ካምፕ ጉዳይ ፣የስደተኞችን ሰብአዊ መብት ለማረጋገጥ ከዓለም አቀፍ ድርጅች ጋር ተባብረን እንሰራለን ካሉ በኃላ አውሮፓ ውስጥ የጥገኝነት ጥያቄ መጠየቅ እንደሚችሉም ጨምረው መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
በሚድትራንያን ባህር 150 ህጻናት የሚገኙባቸው 1,073 ስደተኞች በያዝነው 2017 ዓ.ም ሞተዋል።
ፅሑፉን ያካፍሉ