የአፍሪቃ የስደተኞች ጉባኤ በኡጋንዳ ተካሄደ

ባለፈው ግንቦት ወር ሶስተኛው የፓን-አፍሪካ ፎረም በስደተኞች ጉዳይ የሚመክር ጉባኤ ተካሄደ፡፡ በአፍሪቃ አህጉር የነፃ ዝውውርና ኢንቨስትመንት እንዲጨመርና ይህም የስደተኞች ቁጥር እንደሚቀንስ ታውቋል፡፡

ጉባኤው ከ250 በላይ ተወካዮችና ባለሞያዎችን ያካተተ ሲሆን በስደተኞች ጉዳይና በአለም ላይ ከተከሰተው የስደተኞች ቀውስ የሚመክር ነው፡፡ በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እንዳሉት አፍሪቃ የተትረፈረፈ ባለብዙ የተፈጥሮ ሃፍት ባለቤት ስትሆን ዜጎችዋ በአደገኛ ጉዞ መሞት እንደሌለባቸው በተለይም በሜዲተርያንያን ባህር ጉዞ ለሚጠፋው የሰው ህይወት አሰቃቂ መሆኑ ገልፀዋል፡፡ ይህ ጉዞ ደግሞ በአውሮፓ የተሻለ ህይወት ፍለጋ መሆኑም ገልፀዋል፡፡

ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጨምረው ሲገልፁ የአፍሪቃ አገሮች ለስድተኞች ድንበራቸውን መዝጋት እንደሌለባቸው ገልፀዋል፡፡ አፍሪቃ የስደት አደጋዎች በተለይም በኢንቨስትመንት፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ትምህርትና ንግድን በሚመለከት ወደ መልካም አጋጣሚዎች መለወጥ አለባት፡፡

የኡጋንዳው ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ሩሃካና ሩጉንዳ ለወጣቶች የስራ እድል በሚፈጥሩ ፕሮግራሞች ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ተጨማሪ የስራ እድል ለመፍጠር የአፍሪቃ መንግስታት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎችን ልዩ ትኩረት ማድረግ እንደለባቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ልዩ አማካሪ ሳጃ ጃለው የነፃ ዝውውር የአፍሪቃ ወጣቶችን እንዴት እንደሚጠቅም ሲገልፁ፤ የአለም አቀፍ ማሕበረሰብ የኣፍሪቃ ጥሪትና የአፍሪቃ ፓሰፖርት እንደ ሕጋዊ የጉዞ ሰነድ ሆኖ እንዲያገለግል እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጉባኤው ዋና አላማ በአፍሪካ መንግስታትና በአለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችና ሲቪል ማሕበረሰብ የግሉ ሴክተር በስደተኞች ጉዳይ ዙርያ የጋራ ግንዛቤ አቋም እንዲይዙ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል፡፡