አፍሪካ ውስጥ ያለው ስደትን አስመልክቶ የሚመክር የከፍተኛ አመራሮች የምክክር መድረክ ይፋ ሆነ

አፍሪካ ውስጥ ያለው ህገወጥ ስደት ለመከላከል የሚመክር የከፍተኛ  አመራሮች የምክክር መድረክ በዚህ ወር መጀመሪያ በላይበርያ ተካሄደ፡፡

በዚህ ጉዳይ የሚሰሩ 14 አባላትን ያካተተው የምክክር መድረኩ የተመራው በላይበርያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጀንሰን ሰርሊፍ ሲሆን የመመስረቻ ኣላማውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞችና ስደት ጉዳይ የመጀመሪያና ከፍተኛ አጀንዳው እንዲሆን ማሳመን ነው፡፡

መድረኩ የስደተኞች ሰብአዊ መብትን ለመጠበቅ፣ በሚንቀሳቀሱበት ወቅትም ስደተኞች በተለይም ሴቶች የሚደርስባቸው ችግርና ስቃይ ለመቀነስ በአፍሪካ ሃገራት፣ የየቀጠናዎቹ የኢኮኖሚ ማህበረሰብና አለም አቀፍ የልማት አጋሮች መካከል ያለው ትብብር ለማጠናከር ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሃፊ አብደላ ሃምዶክ አፍሪካውያን በአፍሪካ ውስጥ ያለ ቪዛ እንዲቀሳቀሱ መፍቀድ ጥብቅ የድንበር ቁጥጥሩንና የመንቀሳቀስ ገደቡን እንደሚቀንሰው ገልጸው ይህ ግን ስደተኞች ተገደው እንዲሰደዱ የሚያበረታታና አፍሪካ ከዚህ ዘርፍ የምታገኘውን ጥቅም የሚገድብም ነው ብለዋል፡፡

መድረኩ ለፖሊሲ አውጪዎች ለውይይት የሚቀርብ ዓለም አቀፍ የስደት ጉዳይን የሚመለከት ሃሳብና አጀንዳ የሚቀርጽ ሲሆን በአጠቃላይ ለአፍሪካ እድገት የሚጠቅሙ በስደት ያሉ አፍሪካውያን ስደተኞች የፖለቲካ፣ ፋይናንስና እውቀት ለማስተባበር እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት መድረኩ በሃገራት፣ በየቀጠናውና ዓለም አቀፍ ደረጃ ምክክሮችን በማዘጋጀት በስደት ምክንያት የአፍሪካ አህጉር ያለበትን ክፍተት ላይ የጋራ ፖለቲካዊ መግባባትን የሚፈጥር የመነሻ ሃሳብም ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡