ኢጣሊያ የባህር ሃይል ልዑክ ወደ ሊቢያ ላከች

የጀርመኑ ምግባረ ሰናይ ድርጅት Jugend Rettet ንብረት የሆነችው “ጁቬንታ” የተሰኘችው መርከብ ሰራተኞች በሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ በሜዲትራንያን ባህር ላይ ከእንጨት በተሰራች መርከብ ላይ ተሳፍረው የነበሩ ስደተኞችን ሂወት ታድገዋል፤ ሰኔ 18, 2017፡፡ ፎቶው ሰኔ 18, 2017 በስቴፋኖ ሬላንዲኒ የተነሳ ነው፡፡

በሜዲትራንያን በኩል ወደ ኢጣሊያ የሚመጡ ስደተኞችን ፍሰት መቀነስ ይችል ዘንድ፤ ኢጣሊያ ለሰሜናዊ አፍሪካዊቷ ሀገር የባህር ጠረፍ ጥበቃ ጓድ ድጋፍ የሚሰጥ የባህር ሃይል ልዑክ ወደ ሊቢያ ልካለች፡፡
የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓውሎ ጄንቲሎኒ፤ ተልዕኮው የሚከናነው በተባበሩት መንግስታት የሚደደገፈው የሊቢያ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ጄንቲሎኒ እንዳሉት የተልዕኮው ዋና ዓላማ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቀነስና ከህገወጥ የሰው ዝውውር ጀልባዎች ላይ የታደጓቸውን ስደተኞች ወደ ሊቢያ ለመመለስ ነው፡፡

በኢጣሊያ ምክር ቤት ውስጥ ተልዕኮውን የሚፈቅድ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በተደረገ በደቂቃዎች ውስጥ የኢጣሊያ ተቆጣጣሪ ጀልባ ለተልዕኮ እንዲሰማራ ተደርጓል፡፡ የጀልባዋ ስብስብ ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ጓድ ጋር በመተባበር የታቀዱ የጋራ ተግባራትን ለማከናወን ሃላፊነት የተሰጠው አንድ አነስተኛ ቡድንን ያካተተ ነው፡፡

ለሊቢያው የባህር ጠረፍ ጥበቃ ጓድ የአቅርቦትና እና ጥገና ድጋፍ የሚሰጥ ሌላ ጀልባ በቅርቡ ተቆጣጣሪ ጀልባዋን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢጣሊያ መጀመርያ ላይ ስድስት መርከቦችን ወደ ሊቢያ የውሃ ግዛት ለመላክ አስባ የነበረ ቢሆንም ከትሪፖሊ በኩል ተቃውሞ ስለገጠመው ዕቅዱ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

“ለሊቢያ የባህር ሃይል መርከቦች የጋራ በሆኑ እና በተቀናጁ ተግባራት ላይ ድጋፍ እያደረግን የአቅርቦት፣ የቴክኒክ እና የዘመቻ እርዳታ እናደርጋለን” ብለዋል የመከላከያ ሚኒስተሯ ሮቤርታ ፒኖቲ፡፡

ኢጣሊያ፤ ስደተኞችን የጫኑ ደካማ ጀልባዎች የባህር ላይ ጉዟቸውን ሳይጀምሩ መግታት ይችላል በሚል የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ላይ ተስፋ ጥላበታለች፡፡ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል ይበልጥ ብቁ እንዲሆን ለማድረግ አባላቶቹን በማሰልጠን እና ማጓጓዣዎቹን በማሻሻል ረገድ ኢጣሊያ ንቁ ሚና ስትጫወት ነበር፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት 600,000 የሚደርሱ ስደተኞች ወደ ኢጣሊያ የገቡ ሲሆን፤ ይህም ደግሞ የኢጣሊያ የስደተኞች መቀበያ ማዕከላትን ጫና ውስጥ ያስገባና በሀገሪቱ ፖለቲካዊ መሳሳቦችእንዲጨምሩ አድርጓል፡፡