ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች የስደተኞችን ሂወት አደጋ ላይ ይጥላሉ
የፎቶ ምንጭ: ዩሮፖል፡፡ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን ከመኪኖች ሞተር በላይ ይደብቃሉ፡፡
የአውሮፓ ህብረት ህግ አስከባሪ ኤጀንሲ፤ ዩሮፖል፤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች የአውሮፓ ሀገራት ድንበሮችን አቋርጦ ማለፍ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነባቸው በመምጣቱ ስደተኞችን ከህግ አስከባሪዎች ዓይን ለመከለል ሲሉ የሚጠቀሙባቸውን አዳዲስና አደገኛ መንገዶችን ይፋ አድርጓል፡፡
ዩሮፖል እንዳለው፤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን በተለያዩ መንገዶች በመደበቅ ለአደጋ ያጋልጧቸዋል፤ ከነዚህ ዘዴዎች አንዱ ሰደተኞችን ሞተር በሚገኝበት የመኪናው ክፍል ላይ መደበቅ ነው፡፡ ስደተኞች የድንበር ኬላዎች ላይ ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ በመኪናው ሞተር እና በኮፈኑ መካከል ባለው ክፍተት እንዲደበቁ ይደረጋል፡፡
ይህ ዘዴ እጅግ በጣም አደገኛ ሲሆን በዚህ መልኩ ድንበር የሚያቋርጡ ስደተኞችን ሂወትም አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ከአደጋዎቹ ባሻገር፤ አንድ ምሳሌ ላይ እንደታየው ከሆነ ስደተኞች ለዚሁ አገልግሎት ሲሉ ከቱርክ ወደ ኦስትሪያ ለሚደረግ የአንድ እግር ጉዞ እስከ 7,000 ዩሮ ይከፍላሉ፡፡
በመኪና የሚጓዙ ህገወጥ ስደተኞች የሚገጥሟቸው ሌሎች ለሂወት አስጊ የሆኑ ሁኔታዎች ደግሞ መኪና ውስጥ ታጭቆ መጓጓዝ፣ የአየር እጦት እና ከህግ አስከባሪዎች ለመሸሽ ሲባል የሚደረግ የከፍተኛ ፍጥነት ጉዞ ናቸው፡፡
የዩሮፖል ተቀዳሚ ዳይሬክተር ሮብ ዌንራይት እንዲህ ብለዋል: “ህገወጥ የስደተኞች ዝውውር በአውሮፓ ትልቅና አደገኛ ስራ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከህግ አስከባሪ አካላት የሚደርስባቸው ጫና ከፍ እያለ በመምጣቱ፤ የወንጀል ቡድኖች ተጎጂ ስደተኞችን ድንበር ለማሻገር ሲሉ አብዛኛውን ግዜ ለሂወት አስጊ የሆኑ መዘዞችን የሚያስከትሉ የቀቢፀ ተስፋ ዘዴዎችን ወደ መጠቀም ተሸጋግረዋል፡፡”
የአውሮፓ ህብረት አባል ወደ ሆኑ ሀገራት እና ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላኛው በሚደረገው የስደተኞች ህገወጥ ዝውውር ላይ የተስተዋሉ አዳዲስ እንቅስቃሴዎችንም ዩሮፖል በቅርብ ባወጣው ሪፖርቱላይ ይፋ አድርጓል፡፡ ከነዚህም መካከል ስደተኖችን በህገወጥ መንገድ ለማዘዋወር የቅንጦት ጀልባዎችን (አብዛኛውን ግዜ ፈጣን ባለሞተር ጀልባዎችን) መጠቀም፣ በብላክ ሲ በኩል የህገወጥ ስደት ተለዋጭ መንገድ መከፈቱ እና በምዕራባዊ ሜዲትራንያን ወደ ስፔን የሚደርሱ ህገወጥ ስደተኞች ቁጥር መጨመር ናቸው፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ