21 ኢትዮጵያወያን ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

የፎቶ ምንጭ: ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፡፡ ሊቢያ ውስጥ መሄጃ አጥተው የቆዩ ስደተኞች ጥር 9 ላይ አዲስ አበባ እንደደረሱ፡፡

አምስት ሴቶች የሚገኙባቸው 21 ኢትዮጵያውያን ዜጎች፤ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) እና የኢትዮጵያ መንግስት ከሊቢያ ወጥተው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ባደረጉላቸው ድጋፍ፤ ጥር 9 ላይ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ መለስ አለም እንዳሉት፤ እኚህ ተመላሾች በቅርቡ ወደሀገራቸው እንዲመለሱ እቅድ ከተያዘላቸው በርካታ ተመላሾች የመጀመርያዎቹ ናቸው፡፡ ተጨማሪ 45 ኢትዮጵያውያንም ከቤንጋዚ እና ትሪፖሊ በቅርቡ እንዲመለሱ የጉዞ ሰነዶች ተሰናድቶላቸዋል፡፡
ቃልአቀባዩ በሊቢያ ያለው አለመረጋጋት እና ግጭት በሊቢያ መሄጃ አጥተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚደረገውን ሂደት ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ነገር ግን “መንግስት ዜጎቹን ማነኛውንም ዋጋ ከፍሎ ለማስመለስ ጥረቱን ይቀጥላል” ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
ኢትዮጵያ በሊቢያ የሚገኙ ዜጎቿን ወደ ሀገራቸው መልሳ ለማስመጣት ያላትን ዕቅድ ያስታወቀችው ህዳር 21 ላይ ሲሆን፤ ይህም ሲኤንኤን አፍሪካውያን ስደተኞች ለባርነት በጨረታ ሲሸጡ የሚያሳየውን አስደንጋጭ ዘገባ ማሰራጨቱን ተከትሎ ነው፡፡ ስደተኞቹን ወደሀገራቸው የመመለስ ሂደት ሲያስተባብር የነበረውና በሊቢያ መሄጃ አጥተው ለሚገኙት ስደተኞች አስፈላጊውን የጉዞ ሰነድ የሚሰጠው በካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የአፍሪካ ህብረት ሊቢያ ውስጥ መሄጃ አጥተው የሚገኙትን ስደተኞች ወደየሀገሮቻቸው ለመመለስ ከአጋሮቹ ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በሊቢያ የታገቱ ስደተኞች አብዛኛውን ግዜ እጅግ አስከፊ ለሆኑ አረመኒያዊ ተግባራት የሚጋለጡ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማሰቃየት፣ ያለ ፍላጎት አስገዳጅ የጉልበት ስራ ላይ መሰማራት እና ፆታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡