በ 2018 አጥቢያ ከ 400 በላይ ስደተኞች ሜዲትራንያን ላይ ሞተዋል
የፎቶ ምንጭ: CNN. የሜዲትራንያን ባህር በፈረንጆቹ 2017 ለስደተኞች “እጅግ አደገኛው ድንበር” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
ዓለምአቀፉ የስደት ጉዳዮች ድርጅት (IOM) አዲሱ የፈረንጆች ዓመት ከጠባ ጀምሮ የሜዲትራንያ ባህርን ሲያቋርጡ 404 ስደተኞች ለሞት እንደተዳረጉ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ግዜ ጋር ከነበረው 261 የስደተኞች ሞት ጋር ሲነፃፃር ከፍተኛ ነው፡፡ ተጨማሪ 221 የስደተኞች ሞት በፈረንጆቹ 2018 የመጀመርያዎቹ አንድ ወር ከግማሽ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ የስደተኞች ሞት 625 አድርሶታል፡፡
በዚህ ዓመት እስካሁን ድረስ ባለው ግዜ ወደ ኢጣሊያ የገቡ ስደተኞች ዜግነት ሲታይ፤ አምና ቁጥራቸው ያነሰ ስደተኞች ከሚመጡባቸው ሀገራት ነው በብዛት የመጡት፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የመጡት ከኤርትራ፣ ቱኒዝያ፣ ፓኪስታን፣ ናይጄርያ እና ሊቢያ ነው፡፡
ስደተኞች ባህር አቋርጠው ወደ ኢጣሊያ ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈት የሚዳረጉበት ማካከለኛው የሜዲትራንያን መስመር በ 7 ሳምንታት ውስጥ 365 ሞት በማስተናገድ እጅግ አደገኛው የስደት መስመር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በምዕራባዊው የሜዲትራንያን የስደት መስመር የሚገቡ ስደተኞች ከመካከለኛውና ከምስራቁ መስመር ያነሰ ቢሆንም፤ የምዕራቡ መስመርም ቢሆን እጅግ አደገኛ ነው፡፡ በዚህ የፈረንጆች ዓመት በሰሜን አፍሪካና በስፔን መካከል ባለው ምዕራባዊው የስደት መስመር ሰማኒያ ዘጠኝ ስደተኞች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡
በ 2017 ይፋ የተደረገ አንድ ሪፖርት ላይ IOM ሜዲትራንያን ባህርን “የዓለማችን እጅግ አደገኛው ድንበር” ሲል ሰይሞታል፡፡ በሪፖረቱ ላይ እንደተገለፀው፤ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ 2000 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ቢያንስ 33,761 ስደተኞች ሜዲትራንያን ባህር ላይ ሞተዋል አሊያም የገቡበት አልታወቀም፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ