የአውሮፓ ህብረት የድንበር ኤጀንሲ የስደተኞች ቁጥር ቀንሷል አለ

የአውሮፓ ህብረት የድንበር እና የባህር ጠረፍ ጥበቃ ድርጅት (Frontex) በየዓመቱ የሚያከናውነውን የአደጋ ጥናት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ 2017 የፈረንጆቹ ዓመት በአራት ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛ የስደተኞች ቁጥር የተመዘገበበት ዓመት እንደነበር ይፋ አድርጓል፡፡

አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በ 2016 የፈረንጆቹ ዓመት ከነበረው 511,000 ወደ 204,700 በማሽቆልቆል የ 60% ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ይህ የስደተኞች ቁጥር መቀነስ የተስተዋለው፤ ቱርክን እና ግሪክን በሚያገናኘው ምስራቃዊው የሜዲትራንያን የስደት መስመር እንዲሁም ሊቢያን ከጣልያን ጋር በሚያገናኘው መካከለኛው የሜዲትራንያን መስመር ላይ ነው፡፡ የአውሮፓ ህብረት በ 2016 የፈረንጆቹ ዓመት ግሪክ የሚደርሱ ስደተኞችን መልሶ ወደ ቱርክ ለመላክ ሰምምነት ካደረገ በኃላ፤ በምስራቃዊው መስመር በኩል የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እጅጉን ቀንሷል፡፡

በተጨማሪም በ 2017 የፈረንጆቹ ዓመት መገባደጃ፤ ዓለምን ያስደነገጠውና ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመተባበር ዜጎቿቸውን ወደሀገራቸው እንዲመልሱ የገፋፋቸው በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሊቢያ ውስጥ በአፍሪካውያ ስደተኞች ላይ የሚደርሰው አስከፊ ጥቃት እና ባርነት የሚመለከቱ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ፤ ብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች በበጎ ፈቃዳቸው ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡

ሪፖርቱን በተመለከ ከጣሊያን የዜና አገልግሎት ANSA ጋር ቆይታ ያደረጉት የአውሮፓ ህብረት የድንበር እና የባህር ጠረፍ ጥበቃ ድርጅት (Frontex) ዳይሬክተር እንዳሉት፤ በ 2017 በአጠቃላይ 150,000 ስደተኞች ከአውሮፓ ህብረት ሀገራት ወደሀገራቸው እዲመለሱ ተደርጓል፡፡

እስካሁን ድረስ በ 2018 የፈረንጆቹ ዓመት “የስደተኞች ቁጥር እጅጉን ማሽቆልቆሉን” እና በየካቲት ወር የመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት ጣልያን የገቡ ስደተኞች ቁጥርም 300 ብቻ መሆኑን ለገሪ ጨምረው ተናግረዋል፡፡