በ 2018 የመጀመርያዎቹ ወራት ወደ አውሮፓ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር እጅጉን ቀንሷል
ዓለምአቀፉ የስደት ጉዳዮች ድርጅት (IOM) በ 2018 የመጀመርያዎቹ ዘጠኝ ሳምንታት በባህር ወደ አውሮፓ የገቡ ስደተኞች ቁጥር 10,949 ሲሆን ይህም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ግማሽ ያህል ነው ሲል ይፋ አድርጓል፡፡
ከነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ ስደተኞች መካከለኛውን የሜዲትራንያን መስመር ተጠቅመው ወደ ጣልያን የገቡ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ደግሞ ወደ ግሪክ እና ስፔን የገቡ ናቸው፡፡ የዚህ ዓመት የስደተኞች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ግዜ ጋር ከነበረው 20,051 ሲነፃፀር ግማሽ ያህል ብቻ ነው፡፡
የጣሊያን የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር አሀዝ እንደሚያመለክተው፤ በዚህ ዓመት በባህር ወደ ጣሊያን የገቡ ስደተኞች ቁጥር 5,457 ሲሆን አምና ከነበረው 15,843 ያህል የስደተኞች ቁጥር አንድ ሶስተኛው ነው፡፡ በ 2018 የመጀመርያዎቹ ዘጠኝ ሳምንታት ውስጥ፤ በየቀኑ በአማካይ 83 ስደተኞች ወደ ጣልያን ገብተዋል፡፡ ይህም ደግሞ በ 2017 በየቀኑ የሚገቡ 240 ስደተኞች ጋር ሲነፃፀር አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው፡፡
የጣልያኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ በፈረንጆቹ የካቲት 20 ለ ራይ ኡኖ ቴሌቪዥን ሲናገሩ ጣልያን በአሁኑ ሰዓት በባህር ጠረፎቿ የሚገቡ ስደተኞችን እየተቆጣጠረች ነው ማለታቸውን ANSA የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡ “የስደተኞች ጉዳይ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ሞክረናል፤ አሁን በቁጥጥራችን ስር ነው” ብለዋል ሚኒስትሩ የስደተኞች ቁጥር ለተከታታይ ስምንት ወራት ቅነሳ ማሳየቱን በመጥቀስ፡፡ “የካቲት ወር ላይ፤ ባለፈው የጥር ወር ከነበረው 90% ዝቅ ብሏል፡፡”
ቢያንስ 143,544 ያህል ሀገወጥ ስደተኞች በአጠቃላይ በየቀኑ ደግሞ 2,142 ያህል ስደተኞች ወደ አውሮፓ ይገቡበት ከነበረው 2015 ጋር ሲነፃፀር፤ የዚህ ዓመት የስደተኞች ቁጥር ከ 90% በላይ ቀንሷል፡፡
በፈረንጆቹ መጋቢት 8 ድረስ በዚህ ዓመት የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከአምናው አንድ ሶስተኛ ቢሆንም፤ ወደ ጣሊያን ለመግባት ሲጓዙ በሜድትራንያን ባህር የሞቱ ወይም የጠፉ ስደተኞች ቁጥር ግን በ 15% ብቻ ነው የቀነሰው፤ ይህም 442 ስደተኞች ያክል ሲሆን ባለፈው ዓመት የተመዘገበው ቁጥር ደግሞ 521 ነው፡፡
ከሰሜን አፍሪካ የሚሰደዱ ስደተኞች ቁጥር ካለፈው ሓምሌ ወር ጀምሮ በአስገራሚ ሁኔታ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን ይህም ደግሞ ታጣቂ ቡድኖች ትሪፖሊን መቀመጫው ካደረገው መንግስት ጋር ስደተኞች ሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ለመሄድ የሚያደርጉትን ጉዞ ለመግታት ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው፡፡
ከአውሮፓ ህብረት የቴክኒክ እና የሎጅስቲክ አቅርቦት ድጋፍ ሲደረግለት የነበረው የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል ለስደተኞች ዕርዳታ የሚያደርጉ ሰብአዊ ድርጅቶችን ከውሃ ግዛቱ ላይ በኃይል ገፍቶ ሲያስወጣ የነበረ ሲሆን ስደተኞችንም ከባህር ላይ በመያዝ ወደ ሊቢያ እስር ቤት ሲመልስ ቆይቷል፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በሜዲትራንያን ሲያከናወኑት የነበረ ስራቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡
በዚህ ዓመት በሜዲትራንያን ባህር መጥፋታቸው ከተነገረው 442 ስደተኞች በተጨማሪ፤ 27 ስደተኞች በሰሜን አፍሪካ 56 ስደተኞች ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ በነዚህ የስደት መስመሮች ላይ መሞታቸው ይፋ ሆኗል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ