14,000 የሚጠጉበግሪክየታገቱትስደተኞችወደአገራቸውተመለሱ

በዚህ ዓመት፤ እስካሁን ድረስ ወደ 14 ሺ ገደማ የሚጠጉ በግሪክ ታግተው የነበሩ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ወደየ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ከስደት ተመላሾቹ፤ አብዛኛዎቹ ከሰሜን አፍሪቃ ሃገራት፤ ከማእከላዊ ኤስያና ምስራቃዊ አውሮጳ የመጡ ሲሆኑ ከአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት በተደረገላቸው ድጋፍ ወደየሃገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

የግሪክ ፖሊስ እንዳረጋገጠው እያንዳንዱ ከስደት ተመላሽ ከ500 እስከ 1500 ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደየአገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸው ታውቋል፡፡
የባልካን አገሮች ከ 2016 የመጀመርያዎቹ ወራት አንስቶ ድንበሮቻቸውን ለስድተኞች ዝግ ካደረጉ በኋላ 60 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች በግሪክ ታግተው እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ አብዛኛዎቹ ስደተኞች፤ በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሰላ ትችት በሚያቀርቡባቸውና ለኑሮ አመቺ ባልሆኑ የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት የሂውማን ራይትስ ዎች የቅርብ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ በግሪክ ደሴቶች ውስጥ የሚገኙት የስደተኛ ካምፖች ከሚገጥሟቸው ታላላቅ ችግሮች አንዱ “መታጨቅ”  መሆኑን ለይቶ ያስቀመጠ ሲሆን፤ በተጨማሪም አብዛኞቹ የስደተኛ ካምፖች ማስተናገድ ከሚችሉት የሰው ብዛት ከእጥፍ በላይ የሚልቅ ቁጥር ለማስተናገድ እየታገሉ እንደሚገኙ አክሏል፡፡

የሂውማን ራይትስ ዎች ተወካዮች ባለፈው መስከረም ወር በነዚህ የስደተኛ ካምፖች የዘጠኝ ቀን ጉብኙት ያደረጉ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ የካምፖቹ ኗሪዎች እንደ ፍራሽና ትራስ በመሆን የሚያገለግሏቸውን ጥቂት ብርድልብሶችን ብቻ በመያዝ በድንኳኖች ውስጥ ለመኖር እንደተገደዱ ለማየት ችለዋል፡፡  በተጨማሪም፤ በተለይ ሴቶች ለወሲባዊ ጥቃት እንደሚጋለጡ የጠቆሙ ሲሆን፤ የመንሳቀስ ችግር ያለባቸው ነዋሪዎች ሊገለገሉባቸው የሚችሉ የመታጠቢያ ክፍሎች እንደሌሉም ገልፀዋል፡፡