ሊቢያ ውስጥ የቆዩ ናይጀርያውያን ስደተኞች ወደ ሃገራቸው ተመለሱ
ሊቢያ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል በተለያዩ እስር ቤቶች የቆዩ 164 ናይጀርያውን ስደተኞች በፍቃደኝነት ወደ ሃገራቸው ተመለሱ፡፡
የናይጀሪያ የሚድያ ተቋማት እንደ ዘገቡት ከሆነ እነዚህ በቻርተር አውሮፕላን ሌጎስ ውስጥ የሚገኘው ሙርታላ ሞሃመድ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱት ስደተኞች 97 ወንዶች 54 ሴቶች 11 ህጻናት እና 3 ጨቅላ ህጻናት የሚገኙባቸው ሲሆን በአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) እና በሊቢያ የናይጀርያ ኢምባሲ ትብብር ነው የተመለሱት።
አብዛኛዎቹ ተመላሾች ደስታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው የሃገራቸው መሬት በግንባራቸው ተደፍተው በመሳም ወደ ትውልድ ሃገራቸው በመብቃታቸው ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
“ከሃገሬ ከመዉጣቴ በፊት ህገወጥ አዘዋዋሪው የተሻለ ህይወት ለማግኘት ጣልያን እንደሚያደርሰኝ ሲነግረኝ ቤተሰቦቼም የተሻለ ሂወት እንደሚገጥመኝ አልተመራጠሩም ነበር። ነገር ግን ራሴን ያገኘሁት በሊቢያ ነው። በሊቢያ ውስጥም አዘዋዋሪው አውሮፓ እንደሚወስደኝ በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም አልተገበረውም፡” ብሏል አዲስዋ የተባለ ተመላሽ ስደተኛ፡፡
ለድፍን ዓመት ሊቢያ ውስጥ በእስር ቤት እንደቆየ የተናገረው ስደተኛው “ወደ ሃገሬ ለመመለስ እድሉ ሲገጥመኝ በደስታ ዘለልኩኝ። ሊቢያ ገሃነም ናት። ወደዚያ እንዳይሄዱ ለጠላቶቼም ሳይቀር እጸልያለሁ፡” ብሏል።
ኦውን እና ኢሂስ የተባሉ ሌሎች ተመላሾች በበኩላቸው ሊቢያ ውስጥ እንደባርያ ከተሸጡ በኋላ ለ7 ወራት እስር ቤት ውስጥ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡
ሊቢያ ውስጥ 700,000 ስደተኞች እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙና በዚህ አስቸጋሪ ምክንያትም ብዙዎቹ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ