ተመድ የስደተኞችን ህገወጥ ጉዞ የሚያስተጓጉሉ ዘመቻዎች እንዲካሄዱ ፈቀደ
የፎቶ ምንጭ: UNHCR/ኤፍ. ኖይ
ጥቅምት 5 ላይ፤ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት፤ ሀገራት በሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ ህገወጥ የስደተኞችና የሰዎች ዝውውር እያከናወኑ ነው ብለው በጠረጠሯቸው መርከቦች ላይ ገብተው ምርመራ እንዲያከናውኑ እና በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ የሰጠውን ፍቃድ ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝሞታል፡፡
15-አባላት ያሉት የፀጥታው ምክርቤት በሚስጥር በሰጠው ድምፅ ነው ለሀገራት “ከሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ በሚገኘው ዓለምአቀፍ ባህር ላይ ህገወጥ የስደተኞች ወይም የሰዎች ዝውውር እየተከናወነ ነው ብለው ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት በሚያገኙበት ወቅት መርከቦችን እንዲፈትሹ” የሚያስችላቸውን ይህን ውሳኔ ያደሰው፤ ይህም የሆነው መርከቧ የምታውለበልበው ባንዲራ የየትኛዋ ሀገር እንደሚሆን “ጥሩ የመተማመን ጥረት” ከተደረገ በኋላ ነው፡፡
ውሳኔው “የተደራጁ የወንጀል ቡድኖችን ከተግባራቸው ለማናጠብ እንጂ፤ የግለሰቦችን ሰብአዊ መብቶች ለማንኳሰስ ወይም በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግ እና ዓለምአቀፍ የስደተኞች ህግ ስር ማግኘት የሚገባቸውን ጥበቃ እንዳያገኙ ለመከልከል አይደለም” ሲል የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት አፅንኦት ሰጥቶበታል፡፡
ምክርቤቱ በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ከሊቢያ መንግስት ጋር ተባብረው እንዲሰሩና ሀገሪቷ የድንበሯን ደህንነት መጠበቅ እንድትችል፣ እንዲሁም ደግሞ በየብስ እና በባህር ግዛቶቿ ላይ የሚከናወኑ ህገወጥ የስደተኞች እና የሰዎች ዝውውር ድርጊቶችን መከላከል፣ መመርመር እና ለህግ ማቅረብ እንድትችል ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት በሜዲትራንያን በኩል የሚደረግን ህገወጥ የስደተኞች ጉዞ ለማስቆም በፈረንጆቹ 2015 ‘ዘመቻ ሶፍያ’ በመባል የሚታወቀውን የአውሮፓ ህብረት የባህር ኃይል ዘመቻ እንዲካሄድ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን፤ ዘመቻው እስካሁን ድረስ 117 ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እና 482 ህገወጥ ስደተኞችን የሚያዘዋውሩ መርከቦችን ማስቆም መቻሉን አስታውቋል፡፡ የዘመቻው ኃላፊ በቅርቡ እንዳስታወቁት፤ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር፤ በዚህ የክረምት ወቅት ከሊቢያ የሚነሱ ስደተኞች ቁጥር በ 75% ቀንሷል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ