ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን በሊቢያ የእስር ማዕከላት ያለውን አስከፊ ሁኔታ ገለፀ
ፎቶ: ከትሪፖሊ በስተምዕራብ 59 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሶርማን እስር ቤት የታጎሩ ሴቶችና ህፃናት፡፡ Guillaume Binet/Myop.
ዓለምአቀፉ ሰብአዊ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅት Médecins Sans Frontières (MSF) በሊቢያ የእስር ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች በጣም አስከፊ፣ ጤናማ ባልሆነ እና ለጥቃት በተጋለጠ ሁኔታ እየተሰቃዩ መሆኑን ገለፀ፡፡
በሌላው ስሙ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን እየተባለ የሚጠራው ይህ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው አንድ መግለጫ እንዳስታወቀው ታሳሪዎቹ ለብዙ ዓይነት በሽታዎች መጋለጣቸውንና ብዙዎች ደግሞ በተቅማጥ፣ እከክ እና ቅማል እየተሰቃዩ ነው፡፡
“ታሳሪዎቹ ሁሉም ዓይነት ሰብአዊ ክብራቸው ተገፏል፣ ለጥቃት እና የህክምና እጦት የተጋለጡ ናቸው” ብለዋል የ MSF የህክምና ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዶክተር ሲብየል ሳንግ፡፡
ድርጅቱ ትሪፖሊ አካባቢ በሚገኙ የእስር ማዕከላት ውስጥ የታሰሩ ስደተኞችን የሚያክም አንድ ቡድን አሰማርቶ ስለነበር ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ግዜ ይህን አስከፊ ሁኔታ እንዲታዘብ አስችሎታል፡፡
“ብዙ የእስር ማዕከላት የፀሃይ ብርሃንና ንፋስ በትንሹ ብቻ የሚያስገቡ ሲሆን ከመጠን በላይ የታጨቁም ናቸው፡፡ ለአንድ እስረኛ የሚደርሰው ቦታ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ማታ ላይ ሰዎች እጅና እግራቸውን እንኳን መዘርጋት አይችሉም፡፡ የምግብ እጥረቱ በአዋቂዎች ዘንድ በቂ ምግብ ካለማግኘት የሚመጣ አካላዊ መኮሰስ አስከትሏል፤ አንዳንዶቹ ህመምተኞች አስቸኳይ የህክምና ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል” ብሏል መግለጫው፡፡
MSF የእስር ስርዓቱን “ጎጂና ለጥቃት የሚያጋልጥ” ነው ሲል ይገልፀዋል፡፡ ቁጥጥርና እርምት የመውሰድ አሰራር ባለመኖሩ መሰረታዊ የሆነው አካላዊ ማሰቃየትን እና ተገቢ-ያልሆነ የእስረኞች አያያዝን የሚከለክለው ጥበቃ እንኳን አይከበርም፡፡ መደበኛ የሆነ ምዝገባና ተገቢ የሆነ የመዝገብ-አያያዝ ባለመኖሩ፤ ሰዎች አንዴ ወደ ማእከሉ ከገቡ በኋላ ምን እንደደረሰባቸው ተከታትሎ ማወቅ አይቻልም፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ፤ ስደተኞች ከአንዱ የእስር ማዕከል ወደ ሌላኛው ማዕከል ሊዛወሩ ወይም ደግሞ በይፋ ወደማይገለፁ ቦታዎች ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ምንም ዱኳ ሳይተዉ ይጠፋሉ፡፡
ባለፈው ዓመት፤ የ MSF የህክምና ቡድኖች በትሪፖሊ የሚገኙ ሰባት የተለያዩ የእስር ማዕከላትን በየሳምንቱ ሲጎበኙ ነበር፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ