የተባበሩት መንግስታት በትሪፖሊ የሽግግር ማዕከል ሊከፍት ነው

ትሪፖሊ ውስጥ ስደተኞችን በውስጡ በያዘ የእስር ተቋም ውስጥ ሰዎች ተሰብስበው፡፡ የፎቶ መንጭ: UNHCR/አይሰን ፎንቴን

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጄንሲ (UNHCR) በየዓመቱ እስከ 5,000 የሚደርሱ በሊቢያ ታጉረው የሚገኙ ለአደጋ የተጋለጡ ስደተኞች እና ፍልሰተኞችን ሌላ ቦታ ለማስፈር ወይም ከዚያ ለማስወጣት የሚያስችል የሽግግር ማዕከል በትሪፖሊ ለመክፈት እያቀደ ነው፡፡
የሊቢያ የ UNHCR ተወካይ የሆኑት ሮቤርቶ ሚኖን በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 29 ለሬውቶርስ እንደተናገሩት “በቅርቡ (የፅሁፍ) ፍቃድ እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድጋፍ የሚደረግለት የትሪፖሊው መንግስት ፕሮጀክቱን ቀደም ብሎ በቃል አፅድቆታል፡፡
ቀደም ብሎ የወጣ የ UNHCR መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ ኤጀንሲው ይበልጥ ለአደጋ የተጋለጡትን ቅድሚያ በመስጠት እስከ 1,000 ሰዎች የመያዝ አቅም ያለውና የስደተኞችን የመዘዋወር ነፃነት የሚፈቅድ ክፍት የማቆያ ማዕከል ለመክፈት ዕቅድ አለው፡፡
UNHCR ፆታዊ እና ፆታን-መሰረት ላደረገ ጥቃት ተጋልጠው ለነበሩ ሰዎች የምዝገባ፣ ቅበላ፣ የምግብ አቅርቦት፣ ማህበራዊ አገልግሎቶች፣ ምክር እና ድጋፍ ለመስጠት፤ ይበልጥ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት ደግሞ በሶስተኛ ወገን ሀገራት መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ ፍላጎት አለው፡፡
የሽግግር ማዕከሉ የሚቋቋመው ቀድሞ የስደተኞች ጉዳይ ፖሊስ ማሰልጠኛ በነበረ ተቋም ውስጥ ሲሆን የሚከፈተውም በየዓመቱ እስከ 5,000 የሚደርሱ ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር በማቀድ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት፤ በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች “ዘግናኝ” እና “ኢሰብአዊ” ተብለው የሚገለፁ ሁኔታዎች ባሉባቸው የማጎርያ ማእከላት ውስጥ ነው ተይዘው የሚገኙት፡፡ UNHCR በማጎርያ ማዕከላት ውስጥ ድጋፍ እየሰጠ ሲሆን ከነዚህ ማዕከላት 1,000 ያክል ስደተኞችን ማስፈታትም ችሏል፡፡
በህዳር ወር ስራውን ይጀምራል ተብሎ ዕቅድ በተያዘለት ይህ ማዕከል በሚገኝበት ቦታ ላይ 230 ኔፓላውያን ልዑካን የያዘ አንድ ቡድን በዚህ ሳምንት ውስጥ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ብዙ ሀገራት በትሪፖሊ ቋሚ ዲፕሎማሲያዊ መቀመጫ የሌላቸው በመሆኑ፤ ስደተኞችን ወደ ሌሎች ሀገራት ወስዶ የማስፈር ስራ ውስብስብ ነው፡፡ UNHCR እንዳለው አብዛኞቹን ስደተኞች እና ፍልሰተኞችን ሮማኒያ፣ ስሎቫክያ ወይም ደግሞ ኮስታ ሪካ ውስጥ ወደሚገኙ የሽግግር ማዕከላት ለመውሰድና ከዚያ ላይ ሆነው ወደ ሌላ ሀገራት ለመሄድ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ጥረት ያደርጋል፡፡