የመንግስታቱ የስደተኞች ድርጅት ሪፖርት ስደተኞች በሊቢያ የሚገጥሟቸውን አደጋዎች ዘርዝሯል

በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት UNHCR የታተመው አዲስ ጥናት እንደሚያመለክተው በሊቢያ አቋርጠው ጉዞ የሚያደርጉ ስደተኞች ከማነኛውም ግዜ በበለጠ ለአደጋ ተጋላጭ ሆነው ተገኝተዋል። በመንገዱ ላይ የሚገኝ ያነሰ የድጋፍ አገልግሎትና እየተባባሰ የመጣው የደህንነት ሁኔታ ብዙ ስደተኞችን ለአደጋ ይዳርጋል።

አንደኛው አሳሳቢ ሁኔታ፤ ወደ ሊቢያ የሚደርሱ አብዛኞቹ ስደተኞች እዛው ለመድረሰ እስከ 5,000 የአሜሪከ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ከሚያስከፍሉ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችና ወንጀለኛ ቡድኖች ድጋፍ ይጠይቃሉ። ከዚህም የተነሳ፤ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ንግዱ ከግዜ ወደ ግዜ አደገኛነቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ዋናውን ሚና የሚጫወቱት የታጠቁ ቡድኖች ናቸው።

በአመዛኙ ጉዞውን እያደረጉ ያሉት ወጣት ወንዶች ናቸው። ነገር ግን፤ ለፆታዊ ብዝበዛ የሚዳርግ የሰዎች ዝውውርም እየጨመረ መጥቷል፤ በዚህም ሰለባ የሚሆኑት በተለይ የናይጄርያና የካሜሩን ሴቶች ናቸው። እንደዚሁም ደግሞ በሊቢያ ካለ አዋቂ ሰው ብቻቸውን የሚጓዙ እና ከቤተሰቦቻቸው የተነጠሉ ህፃናት ቁጥርም እየጨመረ ነው።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው ወደ ሊቢያ ከሚጓዙት ግማሽ የሚያክሉት ይህን ጉዞ የሚያደርጉት እዚያው ስራ እናገኛለን በሚል እምነት ቢሆንም፤ በመጨረሻ የሚገጥማቸው ግን ሂወታቸውን-ከሚፈታተኑ አደጋዎች፣ መጠነ ሰፊ ብዝበዛ እና ጥቃት ለማምለጥ መጣጣር ነው።

ዓለምአቀፍ እና ሀገራዊ ድርጅቶች ደቡባዊ ሊቢያ ውስጥ በሚገኙት ባኒ ዋሊድ፣ ራብያና፣ ታዘርቡ እና ኩፊራ የሚባሉት ከተሞችን ጨምሮ ቁልፍ በሆኑ ከተሞች ላይ ለስደተኞች ዕርዳታ በማድረግ ለችግሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርቱ ጠቁሟል።

ሌላው ጥቆማ የድንበር ጥበቃ እና በበረሃው ላይ የታገቱ ስደተኞችን ሂወት ለመታደግ የሚደረጉ ተግባራትን የሚመለከት ነው።

ጥናቱ በቻድ፣ ኒጀር፣ አልጀርያ፣ ቱኒዝያ፣ ሊቢያና ኢጣሊያ ከሚገኙ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ስደተኞች፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሰራተኞች እና የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር የተደረጉ ቃለምልልሶችን አካትቷል።