የኢጣሊያ ሰሜናዊ ሊግ ፓርቲ ስደተኞችን ለማባረር ቃል ገብቷል

የላጋ ኖርድ መሪ የሆኑት ማትዮ ሳልቪኒ
የካቲት 25 ላይ ለሚካሄደው የኢጣሊያ አጠቃላይ ምርጫ እየተደረገ ባለው ፉክክር የቀኝ-ዘመሙ የሰሜን ሊግ ፓርቲ መሪ የሆኑት ማትዮ ሳልቪኒ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በአምስት ዓመታት ግዜ ውስጥ ከሀገራቸው ለማስወጣት ቃል ገብተዋል፡፡

ፓርቲው የመራጮችን ይሁንታ ካገኘ 400,000 የሚገመቱ ስደተኞችን ወደየመጡበት ሀገር መልሶ አንደሚልካቸው ተናግሯል፡፡
“የዘረኝነት ብቸኛው መፍትሄ ስደትን መቆጣጠርና መገደብ ነው፡፡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢጣሊያውያ ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ ናቸው፡፡ ኢጣሊያውያን ዘረኞች አይደሉም፤ ነገር ግን ከቁጥጥር ውጭ የወጣ ስደት ከእርሱ ጋር አዎንታዊ ያልሆኑ ምላሾችን ይዞ ይመጣል፡፡ ያንን ነው መከላከል የምንፈልገው” ብለዋል ሳልቪኒ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (MSF) የተባለው የእርዳታ ድርጅት በመላው ኢጣሊያ በመኖር ላይ የሚገኙ 10,000 የሚሆኑ ስደተኞች ያሉበት “ኢሰብኣዊ” ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡

“ካይን የራቀ” በሚለው በፈረንጆቹ የካቲት 8 በታተመው አዲስ ሪፖርቱ ላይ፤ የኢጣሊያ መንግስት በአሁኑ ሰዓት አገሪቱ ውስጥ በመኖር ላይ የሚገኙና አብዛኞቹ ሮም እና በሮም አቅራቢያ የተጠለሉ ከ 180,000 በላይ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞችን ለማስተናገድ እየታገለ መሆኑን MSF አመልክቷል፡፡

“ስደተኞች ከማህበረሰቡ ጋር ሳይቀላቀሉ እየኖሩ ያሉት በቂ የሆነ የቅበላ ስርዓት ባለመኖሩና ጎጂ የሆነ የድንበር ፖሊሲ በመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ በተጨማሪም፤ በሀገር እና በአካባቢ ደረጃ ስደተኞች ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖራቸውን ቅልቅል ለማፋጠን የተዘጋጁ ፖሊሲዎች አፈፃፀም ደካማ በመሆኑ ነው” ብለዋል የ MSF ባልደረባ የሆኑት ጁሴፔ ዴ ሞላ፡፡
በርካታ ስደተኞች መጠለያ አልባ ስለሆኑ ጎዳናዎች ላይ ነው የሚኖሩት አሊያም ደግሞ መደበኛ ባልሆኑ፣ ህገወጥ በሆነ መንገድ በተተዉ የድሮ ፋብሪካዎች፣ የቢሮ ህንፃዎችና የመኪና ማቆምያ ስፍራዎች ላይ ነው የሚኖሩት፡፡

ከስድስት ወራት በፊት፤ ፖሊስ ከ 800 በላይ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ማእከላዊ ሮም ውስጥ ከሚገኝ ለአራት ዓመታት ሲኖሩበት ከቆዩ የድሮ ፅህፈት ቤት የነበረ አንድ ህንፃ እንዲወጡ አድርጓል፡፡

“ለኛ የሚሆን መፍትሄ እንዳላቸውና አብረናቸው በአውቶቡስ እንድንሄድ ነገሩን” ይላል በረከት አረፈ የተባለ ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ ጣሊያን ውስጥ የኖረ ኤርትራዊ ስደተኛ ለ ጋርዲያን ጋዜጣ ሲናገር፡፡ ነገር ግን ፖሊስ ጣቢያው ላይ ስንደርስ “ህንፃው አሁን ባዶ እንዲሆን ተደርጓል፤ ስራችንን ጨርሰናል አሉን”፡፡ ‘አሁን ታድያ የት እንሂድ’ ብየ ብጠይቃቸው ‘ወይ ጎዳና ላይ ውጡ አሊያም የሆቴል ክፍል ተከራዩ’ አሉን፡፡

ዓለም እየተጓዘ ነው

ዓለማችን በጉዞ ላይ ነው ያለችው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕዝብ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የስደት መከራ እየደረሰባቸው ይገኛል።

የስደት መረጃ፣ ከምንጩ፡ ከመዳረሻና መሸጋገሪያ መንግስታት እስከ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች፣ መገናኛ ብዙሀን፣ ምሁራን እና የስደተኞች የመረጃ ሰንሰለት በተለያዩ ለስደተኞች የማያግዙ ዓላማዋች የተሞላ ነዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ