የቱኒዝያ የባህር ሀይል በመስከረም ወር ከ 550 በላይ ስደተኞችን አስቆመ

የቱኒዝያ የባህር ሀይል በመስከረም ወር በባህር ተጉዞው ወደ ኣውሮፓ ለመግባት የሞከሩ ከ 550 በላይ የቱኒዝያ እና የሰሃራ በታች አፍሪካውያን ስደተኞችን እንዳሰቆመ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቱኒዝያ የባህር ሀይል ከሃገሪቱ ደቡባዊ እና ሰሜናዊ የባህር ዳርቻዎች ስደተኞችን ጭነው የሚነሱ ጀልባዎችን ያስቆመ ሲሆን 555 ሰዎችን ደግሞ በቁጥጥር ስር አውሏል፤ ከዚህ ጋር ሲነፃፀር በነሐሴ ወር 170 ሰዎች ብቻ ነበር የተያዙት፡፡
“የአካባቢው የአየር ሁኔታ በመሻሻሉ እና ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከቱኒዝያ የሚደረግ ጉዞ ከሌሎች መዳረሻዎች ይልቅ አስተማማኝ ነው በማለት የማሳመን ስራ በሚሰሩበት በዚህ ወቅት እየጨመሩ የመጡትን ብዙ ሙከራዎች ማክሸፍ ላይ ተሳክቶልናል፡፡” ብለዋል የቱኒዚያው ብሄራዊ ዘብ ኮሎኔል ሜጀር ካሊፋ ቺባኒ፡፡
የቱኒዝያ የባህር ሀይል በፈረንጆቹ መስከረም 30፤ ከከርከናህ አቅራቢያ በደቡብ ምስራቅ ጠረፍ አካባቢ ጀልባቸው ሲሰምጥባቸው የነበሩ 98 ቱኒዝያውያንን መታደግ መቻሉንም ብሄራዊ ዘቡ አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተለየ፤ አሁንም በሃገሪቱ ደቡብ ምስራቅ ጠረፍ አካባቢ፤ ከ ዛርዚስ አቅራቢያ ከአራት ጀልባዎች ላይ የታደጓቸውን 43 ስደተኞችን ማሰራቸውን የቱኒዝያ መከላከያ ሰራዊት ተናግረዋል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚለው፤ ሜዲትራንያንን አቋርጠው ወደ ኢጣሊያ ለመግባት በባህር በመጓዝ ላይ ሳሉ ወይም ጉዞ ለመጀመር እንደተሳፈሩ ሂወታቸውን ከታደጉላቸው ወይም ካስቆሟቸው ስደተኞች መሃል ሴቶች እና ህፃናት ይገኙባቸዋል፡፡
የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል ከኢጣሊያ በሚሰጠው ቴክኒካዊ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በመታገዝ ስደት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በሚያደርግበት በዚህ ወቅት፤ ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ወደ ኣውሮፓ የሚጓዙ ጀልባዎችን ጉዞ ለማስጀመር የቱኒዝያን የባህር ጠረፍ አዘውትረው መጠቀም ጀምረዋል፡፡
የኢጣልያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ሊብያ እና ቱኒዝያ ህገ ወጥ የስደተኞችን ፍሰት ለመቆጣጠር ያስችላቸው ዘንድ የ 60 ሚልዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አስታውቋል፡፡