የነፍስ አድን መርከብ ሰራተኞች በዓለምአቀፍ ውሃ ላይ እንዳለን የሊቢያ የባህር ጥበቃ ገባብን አሉ

የአንዲት ሰብአዊ ዕርዳታ ሰጪ መርከብ ሰራተኞች የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 26 በዓለምአቀፍ የውሃ ግዛት ላይ እንዳሉ እንደገባባቸው እና ከእንጨት ጀልባ ላይ የታደጓቸውን 70 ስደተኞች አሳልፈው እንዲሰጡ እንደጠየቋቸው አስታውቀዋል፡፡

ሊብያውያኖቹ መርከቧ ላይ የነበሩትን ሰራተኞች ግዛታቸው እንደሆነ ነገረው ከዚያም በኋላ ወደ ሰማይ ወይም ወደ ባህሩ መሳርያ ተኩሰዋል፡፡

“ስደተኞችን ወደ ሊቢያ እንደማንመልስ ነገርናቸው፡፡ ከጥቂት ግዜ በኋላ፤ ተስፋ ቆረጡ” ብለዋል የመጀመርያ የነፍስ አድን ስራውን ማክሰኞ ላይ ያከናወነውና መቀመጫውን በጀርመን ያደረገው የዕርዳታ ድርጅት ‘ሚሽን ላይፍላይን’ ቃል አቀባይ የሆኑት አክሴል ስቴር ለሬውቶርስ ሲናገሩ፡፡

በትሪፖሊ የሚገኙት የሊብያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ቃልአቀባይ ጉዳዩን እያጣራሁ ነው በማለት አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፤ ስደተኞችን የመታደግ ስራ የሚያስተባብረው የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ በበኩሉ በተደጋጋሚ የተደረገለትን የስልክ ጥሪ አልመለሰም፤ እንደሬውተርስ ዘገባ፡፡

ይህ ክስተት በሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ እና በሰብአዊ እርዳታ ሰጪ መርከቦች መካከል እያጋጠሙ ካሉ ተመሳሳይ ክስተቶች በቅርቡ የተፈፀመው ነው፡፡

ሌላ በቅርቡ ባጋጠመ ክስተት፤ አንዲት የስፔን ነፍስ አድን መርከብ በዓለምአቀፍ የውሃ ግዛት ላይ እንዳለች በሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ እንድትቆም ተደርጋ ወደ ትሪፖሊ አቅጣጫ እንድትጓዝ አሊያም ደግሞ ተኩስ እንደሚከፈትባት ትዕዛዝ ተላልፎባት የነበረ ሲሆን፤ በመጨረሻ ግን እንድትሄድ ተፈቅዶላታለ፡፡
ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ጋር እየጨመረ የመጣውን መቃቃር ምክንያት በማድረግ፤ ሴቭ ዘ ችልድረን፣ ሜዲስንስ ሳንስ ፈሮንትየርስ፣ የጀርመኑ ሲ አይ እና የማልታው ሚግራንት ኦፍሾር ኤይድ ስቴሽን የተባሉ አራት ታላላቅ ሰብአዊ ዕርዳታ ሰጪ ደርጅቶች በሜዲትራንያን ላይ የሚያከናውኑትን የነፍስ አድን ስራ አቁመዋል፡፡

ኢጣሊያ በሚዲትራንያን በኩል የሚደረገውን የስደተኞች ፍሰት ለመቀነስ ያስችል ዘንድ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይልን በስልጠና እና መሳርያዎች ስትደግፍ ነበር፡፡ አለምአቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት እንደሚለው፤ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል በዚህ ዓመት እስካሁን ድረስ 16,567 ሰዎች ገና የእርዳታ ድርጅቶች ሳይታደጓቸውና ወደ ኢጣሊያ ሳይወሰዱ ማስቆም ችሏል፡፡

ወደ ኢጣሊያ የባህር ዳርቻዎች የሚደርሱ የስደተኞች ቁጥር ቀንሷል፤ ነገር ግን ብዙዎች አሁንም ቢሆን ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሲሉ ሂወታቸውን አደጋ ላይ እየጣሉ ነው፡፡

“አሁን ሊቢያ ውስጥ ምንም ስራ የሚባል ነገር የለም፤ ለጥቃት ትጋለጣለህ” ሲል የ 26-ዓመቱ ሊቢያዊ ከባህር ላይ ለታደጉት የ SOS Mediterranee’s Aquarius ሰራተኞች ተናግሯል፡፡ “ሊቢያ ውስጥ መኖር በፍፁም የማይቻል ነገር ነው፤ በጣም አደገኛ ሆኗል፡፡”