የአውሮፓ ህብረት 50,000 ስደተኞችን ሊያሰፍር፤ ብዙዎችን ደግሞ ሊመልስ ነው
የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 50,000 ለችግር የተጋለጡ የመካከለኛው ምስራቅ፣ ሰሜን አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞችን ተቀብሎ ለማስፈር የያዙትን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በፈረንጆቹ መስከረም 27 ቀን ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ጥቅምት 2019 ላይ ወደ አውሮፓ እንዲገቡ የሚደረጉ በተለይም ለችግር የተጋለጡ ቢያንስ 50,000 ተጨማሪ ስደተኞችን ለማስፈር የሚያስችል አዲስ ዕቅድ እያዘጋጀ ነው፡፡
ከቱርክና ከመካከለኛው ምስራቅ የሚደረገው ስደተኞችን ተቀብሎ የማስፈር ስራ የሚቀጥል ሲሆን፤ ከሰሜን አፍሪካ እና አፍሪካ ቀንድ በተለይም ሊቢያ፣ ግብፅ፣ ኒጀር፣ ሱዳን፣ ቻድ እና ኢትዮጵያ ስደተኞችን የመቀበል አሰራር ላይ የተለየ ትኩረት ይደረግበታል፡፡
የአውሮፓ ኮሚሽን፤ በዚሁ ስደተኞችን ተቀብሎ የማስፈር ሂደት ላይ አባል ሀገራቱን ለመደገፍ 500 ሚልዮን ዩሮ መድቧል፡፡
በተጨማሪም፤ የአውሮፓ ህብረት ስደተኞችን ወደየሀገራቸው የመመለስ ፖሊሲውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉትን አዳዲስ እርምጃዎች ለመጀመር አንዲሁም ደግሞ በሁሉም አቅጣጫዎች ስደተኞችን ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችን ከፍ ለማድረግ አቅዷል፤ በዚህም እስከ 1.5 ሚልዮን የሚገመቱ ሰዎች በቅርቡ ወደየሀገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ስደተኞችን የመመለስ ፖሊሲ የሚገልፅ አንድ ፅሁፍ እንዲህ ሲል አስፍሯል “ስራዎቹን ለማከናወን ነፃነት የተሰጠውና የተጠናከረ ስደተኞችን የሚመልስ ፅህፈት ቤት፤ አዳዲሶቹ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ መተግበራቸውን እና ጥቅም ላይ መዋላቸውን ያረጋግጣል፡፡”
የአውሮፓ ህብረት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አብራሞፖውሎስ እንዲህ ብለዋል፡ “እኛ ያቀረብነው ዕቅድ፤ በአውሮፓ የድንበር እና የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኤጀንሲ ውስጥ እውነተኛና ሊሰራ የሚችል የአውሮፓ ህብረት ስደተኞችን መመለሻ ማዕከል ለመፍጠር ነው፡፡ አንዲሁም ደግሞ አደገኛ ህገወጥ ስደትን በመምረጥ ፋንታ ሊያገለግሉ የሚችሉ እውነተኛ አማራጮችን መክፈት እንፈልጋለን”
ፅሑፉን ያካፍሉ