የሊቢያ ጠረፍ ጥበቃ የሚያደርገው የስደተኞችን ጉዞ የማስተጓጎል እንቅስቃሴ መደበኛ እየሆነ ነው
የፎቶ ምንጭ: ሬውቶርስ/አህመድ ጃዳላህ
በሊቢያ የባህር ሃይል ከተያዙ በኋላ ወደ ባህር ሃይል ማዘዣ ጣቢያ የተወሰዱ ስደተኞች፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት፤ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል በሜዲትራንያን ባህር ላይ ሲጓዙ የነበሩ ቢያንስ 450 ስደተኞችን የያዘ ሲሆን ወደ ሊቢያ እንዲመለሱም አድርጓል፡፡
በፈረንጆቹ ጥቅምት 31 ቀን፤ 40 ሴቶችና 19 ህፃናትን ጨምሮ 299 ስደተኞች በሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ ሞተር በሌላቸው ሁለት የጎማ ጀልባዎች ተጭነው ባህር ላይ ሲንሳፈፉ ተገኝተዋል፡፡ የጠረፍ ጥበቃ ኃይሉ ቃል አቀባይ የሆኑት አዩብ ቃሲም እንዳሉት ስደተኞቹ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ናቸው፡፡
የጠረፍ ጥበቃ ኃይሉ ስደተኞቹን ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት በተገኘበት ትሪፖሊ ወደሚገኘው የባህር ሃይል ማዘዣ ጣቢያ እንዲዘዋወሩ ያደረጋቸው ሲሆን፤ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ታጆራ የህገወጥ ስደተኞች መጠለያ ማዕከል እንዲረከባቸው ተደርገዋል፡፡
በፈረንጆቹ ህዳር 4 ቀን፤ ከመጠን በላይ በታጨቀች የጎማ ጀልባ ተጭነው ሜዲትራንያንን በማቋረጥ ወደ ኢጣሊያ ለመድረስ የሞከሩ ከ 150 በላይ ስደተኞችን የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይሉ በቁጥጥር ስር አውሏል ሲል ሬውቶርስ ዘግቧል፡፡
ስደተኞቹ በሊቢያ የባህር ኃይል መርከብ ተጭነው በሚወሰዱበት ወቅት፤ የስደተኞቹ ጀልባ ቅኝት ስታደርግ ከነበረችው የኢጣሊያ ጠረፍ ጥበቃ መርከብ በቅርብ ርቀት ላይ ነበረች፡፡
“ስደተኞቹን ከሞት ታድገናቸዋል” ብሏል ስደተኞቹን መልሳ ወደ ትሪፖሊ የወሰደችው የሊቢያ መርከብ ካፒቴን፡፡
ስደተኞች ዓለምአቀፍ የነፍስ አድን መርከቦች አቅራቢያ ከመድረሳቸው በፊት በቁጥጥር ስር የማዋል እንቅስቃሴውን የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው፤ ይህም ደግሞ ከኢጣሊያና ከአውሮፓ ህብረት በሚያገኘው የስልጠና እና የቴክኒክ ድጋፍ ነው፡፡
ስደተኞች ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላ፤ አንዳንዶቹ በበጎ ፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው የመመለስ ዕድል ወደሚያገኙባቸው የእስር ማዕከላት ከመወሰዳቸው በፊት በዓለምአቀፍ ድርጅቶች እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡
“በጣም ተሰቃይቻለሁ – መጠለፍ፤ ለገንዘብ ሲባል መታፈን ደርሶብኛል” በማለት የ 20 ዓመቱ ናይጄርያዊ ክሪስቶፈር ዳንኤል ለሬውቶርስ ተናግሯል፡፡ “እነሱ [ጠባቂዎቹ] ዓይኔን ጨፍነው ብር እንድሰጣቸው አስገድደውኛል” ብሏል ባለፈው ዓመት በደቡባዊቷ የ ሳብሃ ከተማ ስላሳለፈው የምርኮ ግዜ ሲያወራ፡፡
“ምን ማለት እንዳለብኝም ሆነ ምን እንደማደርግ አላውቅም፡፡ ያንን ሁላ ብር አባክኜ – ቤተሰቦቼን ምንድን ነው የምላቸው?”
ፅሑፉን ያካፍሉ