በአውሮፓ ዘረኝነትን የሚቃወሙ ሰልፎች እየተደረጉ ነው
የተባበሩት መንግስታት የፀረ ዘረኝነት ሳምንትን ምክንያት በማድረግ በፈረንጆቹ መጋቢት 17 ዘረኝትን በመቃወም ለንደን ከተማ ላይ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች መፈክሮችን እና ፖስተሮችን ይዘው ይታያሉ፡፡
በመላው አውሮፓ በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመጤዎች ጥላቻ፣ ዘርአዊና ሃይማኖታዊ መገለለልን በመቃወም እንዲሁም ደግሞ ለስደተኞች መብት ድጋፋቸውን በመግለፅ በተባበሩት መንግስታት የአውሮፓ የፀረ ዘረኝነት ሳምንት (በፈረንጆቹ መጋቢት 17 እስከ 25 ) በሚከበርበት ወቅት ሰላማዊ ሰልፎችን አድርገዋል፡፡
በእንግሊዝ፤ የለንደን ሰልፈኞች ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ የመጣውን የቀኝ ዘመም አክራሪነትን እና ከእርሱ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን የጥላቻ ወንጀሎች መበራከትን በመቃወም፤ “ስደተኞችን እዚህ በበጎ እንቀበላቸዋለን” እንዲሁም “ዘረኛ ጥቃቶች ይቁሙ” የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
በቬና ደግሞ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች “ዘረኝነትን ፀጥ እናስብል” የሚልና ሌሎች ፅሁፎችን አንግበው አደባባይ ወጥተዋል፡፡
የኦስትርያ ዜጎች በበኩላቸው የኦስትርያው ቀኝ-ዘመም ፍሪደም ፓርቲ ከወግ አጥባቂው ፒፕልስ ፓርቲ ጋር ወደ ጥምር መንግስት በገባ በጥቂት ወራት ውስጥ ነው ተቃውሟቸውን የገለፁት፡፡ ቀኝ ዘመሙ ፍሪደም ፓርቲ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ጥብቅ የስደተኞች ቁጥጥር እንዲደረግና የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞች ቶሎ ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረግ እንዳለበት አበክሮ ሲቀሰቅስ ነበር፡፡
በፈረንሳይ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፤ ፖሊስ ስደተኞች ላይ የሚወስደውን የጭካኔ ተግባር በመኮነን ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችም በተሻለ መልኩ እንዲስተናገዱ ጠይቀዋል፡፡ ይህም የሆነው፤ በቅርቡ የተከናወነ አንድ ጥናት ላይ፤ በፓሪስ በችግር የሚኖሩ ስደተኞች በፈረንሳውያን ዜጎች አካላዊና ፆታዊ ጥቃት በፖሊስም የጭካኔ ተግባር እንደተፈፀመባቸው ከገለፁ በኋላ ነው፡፡
በአቴንስ ደግሞ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግሪካውያን “ድንበሩን ክፈቱ” የሚል መፈክር እያሰሙ እንዲሁም ዘረኝነትን የሚቃወሙ መልዕክቶችን እና የአውሮፓ ህብረት የስደት ፖሊሲን የሚኮንኑ ፅሁፎችን በመያዝ ወደ አደባባዮች ተመዋል፡፡
እንዲሁም በፖላንድ፤ በዋርሳው እና ሌሎች ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቃውሞ ህዝባዊ ትእይንት ያዘጋጁ ሲሆን በማህበራዊ ሚድያ እና በአገሪቱ ህዝባዊ ውይይቶች ላይ እየጨመረ የመጣውን ዘረኝነት እና ፀረ አይሁድ አስተሳሰብን ተቃውመዋል፡፡
ይህ ዓመታዊ ዝግጅት በፈረንጆቹ አቆጣጠር መጋቢት 21/ 1960 ላይ፤ ቆየት ብሎ የሻርፕቪለ እልቂት በመባል የተሰየመው፤ በደቡብ አፍሪካ የተገደሉት 69 የፀረ-አፓርታይድ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ለመዘከር የሚደረግ ሲሆን፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ 1966 የፈረንጆቹ አቆጣጠር ዓለምአቀፍ ዘርአዊ መገለልን የማስወገድ ቀን ተብሎ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ