ኢትዮጵያ ለስደተኞች የትምህርት፣ ስልጠና እና የስራ እድሎችን ልታሻሽል ነው
የፎቶ ምንጭ: ሬውቶርስ፡፡ ወጣት ኤርትራውያን ስደተኞች ሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኘው የማይ-ዓይኒ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ ሁለገብ የስደተኞች ጉዳይ አሰራር ይፋ ያደረገች ሲሆን፤ ዓላማውም በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሂወት ለማሻሻል ነው፡፡
ሰነዱ እንደሚያመላክተው፤ የዚህ አሰራር አንዱ ቁልፍ ዓላማ ስደተኞች መስራት እንዲችሉ ለማድረግ፣ እራሳቸውን እንዲደግፉ እና በመንግስት ወይም የዕርዳታ ድርጅቶች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንዲቀንስ ማስቻል ነው፡፡
ስደተኞች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ፣ እንዲሁም የክህሎትና የሞያ ስልጠናዎች እንዲሰጣቸው ለማድረግ ኢትዮጵያ አቅዳለች፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ፍፁም አረጋ እንዳሉት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለስደተኞች የስራ ዕድል ለመፍጠር የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራ ነው፡፡
በአላጌ፣ ድሬዳዋ እና መቀለ ከተሞች ውስጥ በሚገነቡት ሶስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 30,000 ያክል የስራ ዕድሎች ይኖራሉ ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተጨማሪም ስደተኞች ከካምፖች ወጥተው እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን ረቂቅ አዋጅ እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደምታቀርብም ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ሰዓት ከ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሶማልያ እና የመን የመጡ ከ 850,000 በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን ተቀብሎ እያስተናገደ ነው፡፡
ይህች ምስራቅ አፍሪካዊት ሀገር፤ በቅርቡ ለስደተኞች የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት መስጠት የጀመረች ሲሆን ሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙት 26 የስደተኞች ካምፖችና በብዛት ስደተኞች በሚኖሩባቸው ሌሎች ሰባት ስፍራዎች ምዝገባ የሚከናወንባቸው ፅህፈት ቤቶችን ማቋቋማዋን UNHCR አስታውቋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ