ጣሊያን ለአፍሪካ የሚደረግ ተጨማሪ የ 80 ሚልዮን ዩሮ ድጋፍ ይፋ አደረገች

የፎቶ ምንጭ: አንጀሊኖ አልፋኖ/ MAECI የ “የጋራ ሃላፊነት ለጋራ ዓለማ — ወዳጅነት እና ደህንነት” በሚለው ሁለተኛው ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሚኒስትሮች፡፡
ከአፍሪካ የሚደረገውን ህገወጥ ስደት ለመዋጋት የተዘጋጀውና ለአፍሪካ የሚደረገው የ 200 ሚልዮን ዩሮ ድጋፍ ላይ ተጨማሪ 80 ሚልዮን ዩሮ እንደምትሰጥ ጣሊያን ይፋ አድርጋለች፡፡
የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንጀሊኖ አለፋኖ ይህን የገንዘብ ድጋፍ ይፋ ያደረጉት በፈረንጆቹ የካቲት 6 ሮም ውስጥ ከአፍሪካና ከአውሮፓ ህብረት የመጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተሳተፉበት ጉባኤ ላይ ነው፡፡
“ስደተኞች የሚመጡባቸው ማህበረሰቦችና የሚተላለፉባቸው ሀገራት ላይ የሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ ኢንቨስመንቶችን እንደገና መጀመር እንፈልጋለን” ብለዋል አልፋኖ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያቤቱ የትዊተር ገፅ ላይ፡፡ “ጣሊያን ለአፍሪካ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ላይ ተጨማሪ 80 ሚልዮን ዩሮ ለመስጠት ወስናለች፡፡”
ይህ ከጣሊያን ለአፍሪካ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ የተጀመረው በፈረንጆቹ ጥር 2017 ላይ ሲሆን ዓላማውም “ህገወጥ ስደትን ለመዋጋት፣ ስደተኞች የሚያደርጉትን ጉዞ ለመግታት እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማጥፋት” ነው፡፡
የስደተኞች መተላለፍያና መዳረሻ ከሆኑ የአፍሪካና የአውሮፓ ሀገራት የመጡ ሚኒስትሮች ከፈረንጆቹ ሓምሌ 6 / 2017 ወዲህ ለሁለተኛ ግዜ በተካሄደው “የጋራ ሃላፊነት ለጋራ ዓላማ — ወዳጅነትና ደህንነት”በሚል ርዕስ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ተሳታፉ ነበሩ፡፡
ከአልጀርያ፣ ቻድ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ሊቢያ፣ ማልታ፣ ኔዘርላንድ፣ ኒጀር፣ ስፔን፣ ሱዳን፣ ቱኒዝያ እና በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ህብረት ምክርቤት ሊቀመንበርነት ይዛ የምትገኘው ቡልጋሪያ የመጡ ሚኒስትሮች በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል፡፡ የተባበረት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR)፣ የተባበሩት መንግስታት የስደት ጉዳዮች ኤጀንሲ (IOM)፣ እንዲሁም የአውሮፓ ደህንነትና ትብብር ድርጅት (OSCE) በጉባኤው ለይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በጉባኤው መዝጊያ ላይ፤ተሳታፊ የሆኑ ሀገራት “ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችና፣ ህገወጥ ስደተኞች በተለይም ሴቶችና ህፃናት የሚደርስባቸው ስቃይ፣ ጥቃት እና ብዝበዛ እንዲሁም ደግሞ በሚደረገው ጉዞ ላይ የሚጠፋው ሂወት እጅጉን እንደሚያሳስባቸው” ገልፀዋል፡፡
ሀገራቱ “ስደተኞች ከሚተላለፉባቸው የአፍሪካ ሀገራት” ጋር በመቀናጀት “ዓለምአቀፍ ትብብር እንዲጠናከር” እና “የህገወጥ ስደት መከላከል እና የደንበር ጥበቃ ቁጥጥር እንዲሻሻል” ጥሪ አቅርበዋል፡፡