ስደተኞችን ስትቀበል የነበረችው የጀርመን ከተማ ከንግዲህ ጥገኝነት ጠያቂዎችን አታስተናግድም
የጀርመንዋ ከተማ – ፒርማሰንስ
የጀርመን ሪንላንድ-ፓላቲኔት ግዛት የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን በመጥቀስ ዶቼ ቬሌ የዜና አውታር እንደዘገበው፤ የፒርማሰንስ ከተማ ከእንግዲህ ወዲያ አዳዲስ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንድትቀበል ግዴታ አይኖርባትም፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው፤ ብሄራዊ መንግስቱና የማህበረሰቡ መሪዎች ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ሲሆን፤ የማህበረሰብ መሪዎቹ ከተማቸው ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከማህበረሰቡ ጋር ቀላቅሎ ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ሃብት እንደሌላት ለረዥም ግዜ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡
“ለፒርማሰንስ ከተማ የአጭር-ግዜ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን፤ ምክንያቱም ከተማዋ ያለችበት ሁኔታ ለየት ያለ ነው፡፡” ብለዋል ስደተኞችን እና ነባር ማህበረሰቡን የማቀላቀል ጉዳዮች የሚከታተሉት ሚኒስቴር አኔ ስፒገል፡፡
የከተማዋ ከንቲባ በርሃርድ መቲስ በበኩላቸው ውሳኔው መደረጉ እንዳስደሰታቸውና ብሄራዊ መንግስቱም “እፎይታ ስለሰጠን” እናመሰግናለን ሲሉ ለፈረንሳዩ የዜና አውታር AFP ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ድረስ፤ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ፒራማሰንስ ሲላኩ የነበሩት ለመኖርያ የሚሆኑ በርካታ ክፍት አፓርትመንቶች ስለነበሩ ነበር፡፡ ነገር ግን፤ ከተማዋ የገጠማት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ለስደተኞቹ የሚያስፈልገውን አገልግሎት ማቅረብ ከባድ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን፤ አፓርትመንቶቹ ክፍት እንዲሆኑ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከልም ይሄው የኢኮኖሚ ችግር አንዱ ነው፡፡
ይህች 40,000 ነዋሪዎች ያሏት ከተማ እስከ 1,300 ያክል ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ አስተናግዳለች፤ ከነዚህም መካከል አብዛኞቹ ጥያቂያቸው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የከተማዋ ከንቲባ የሆኑት ማቲስ “የማንቂያ ደወል” መስማት የጀመሩት ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ መሆኑን፤ ይህም በጎፈቃደኞች እና መምህራን በከተማዋ ካለው በርካታ የስደኞች ቁጥር የተነሳ ተግባሮቻቸውን ለማከናወን ድጋፍ እንደሚሹ ካጤኑ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሰፒገል ደገሞ የፒርማሰንስ “የተለየ ጉዳይ” ቢሆንም፤ በርካታ በመላው ጀርመን የሚገኙ ከተሞች ተጨማሪ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን ማስተናገድ አንችልም የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡
ባለፈው ወር፤ ኮትበስ የምትባለው ከተማ አዲስ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን እንደማትቀበል ይፋ አድርጋለች፡፡ በተመሳሳይ፤ ሳልዚግተር፣ ዴልሞንሆርስት እና ዊልሀልምሻቨን ከተሞች ባለፈው ዓመት ክልከላ ለማኖር የተነሳሱ ሲሆን፤ ለዚህም ምክንያት አድርገው የጠቀሱት የሚመጡትን ስደተኞች ማስተናገድ የሚያስችል በቂ ሀብት እንደሌላቸው ነው፡፡
በሪንላንድ-ፓላቲኔት ግዛት የህግ አርቃቂ አካል ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ከተሞች የፒርማሰንስ ያክል ችግር እየገጠማቸው መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጥ አገር-አቀፍ ዳሰሳ እንዲደረግ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡
ፅሑፉን ያካፍሉ