ተበዳዮቹን ያሰቃየው ሶማልያዊ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ ኢጣሊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ

አንድ ሶማልያዊ በደቡባዊቷ የኢጣሊያ ደሴት ላምፔዱሳ በቁጥጥር ስር ውሏል፤ የቀረበበት ክስም በሊቢያ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመድፈር እና በማሰቃየት ወንጀል ነው።

የደሴቷ ፖሊስ እንዳለው የ 23 ዓመት ዕድሜ ያለው ተጠርጣሪው መሃመድ አህመድ ጣሂር፤ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመደብደብ “ሃሴት ያደርግ” ነበር። ስደተኞች ጣሂርን በደቡባዊ-ምስራቅ የሊቢያ ክልል ውስጥ በምትገኘው ኩፍራ የተባለች ቦታ ላይ በሚገኘው ማጎርያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ አሰቃይ ነው ሲሉ ለይተውታል።

ከመጋቢት ወር ወዲህ፤ ሊቢያ የሚገኙ ስደተኞችን በማሰቃየት ተጠርጥረው ኢጣልያ ውስጥ በቁጥጥር ሰር ከዋሉት ሰዎች መካከል ጣሂር ስድስተኛው ሰው ነው፤ ሀገሪቱ ውስጥ እየቀጠለ ያለውን የእርስበርስ ጦርነት ቀውስን ተገን በማድረግ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች እና አሸጋጋሪ ወሮበላ ቡድኖች አደገኛ ንግድ አቋቁመዋል።

“ላምፔዱሳ እንደደረሰ ያወቁትን ሰዎች ዝም እንዲሉ አስፈራርቷቸው ነበር፤ ነገር ግን እሱን ለፖሊስ ለይተው ለማስታወቅ ድፍረቱ ነበራቸው” ብለዋል ምርመራውን ያካሄደው ቡድን የመሩትና በቁጥጥር ስር ያዋሉት የፖሊስ መኮንን ጂዮቫኒ ሚናርዲ።

ሚናርዲ እንዳሉት ጣሂር  ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ጠለፋ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ግድያ እና ህገወጥ ስደትን በማመቻቸት ላይ በተሰማራ የታጠቀ ድንበር-ዘለል የወንጀለኞች ድርጅት ውስጥ ተሳታፊ ነበር። የቀረበበት ክስ ስደተኞችን በጎማ ቱቦ መደብደብ፣ በነዳጅ ማቃጠል እና በመሳርያ ማስፈራራት የሚሉ ይገኙበታል።

“ስደተኞችን ይደበድባል። እኛን በማዋረድ እና በማንአለብኝነቱ ሃሴት ያደርግ ነበር። አንድ ግዜ አስታውሳለሁ፤ የማጎርያው ባለቤት የሆነው ሊቢያዊው ሰውየ ተቆጥቶት ነበር፤ ምክንያቱም በመጥፎ ሁኔታ ስለሚመታን ከድብደባው የተነሳ ሰዎች ይሞቱ ነበር” ብሏል አንድ ተበዳይ።