ስደተኞች ወደ አውሮፓ ይወሰዳሉ የሚል የውሸት ጭምጭምታ ወደ ኒጀር የሚሄዱ ስደተኞችን ቁጥር ጨምሮታል

ከኒጀር ወደ አውሮፓ የሚደረግ ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞ አለ የሚለው የውሸት ጭምጭምታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ኒጀር ውስጥ ወደምትገኘው የአጋዴዝ ከተማ እንዲተሙ ምክንያት ሆኗል ሲል InfoMigrants የተባለው ድረገፅ ዘግቧል፡፡
ከነዚህ ጭምጭምታዎች አንዱ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ማነኛውንም ሰው ከአጋዴዝ ወደ አውሮፓ በገፍ እየወሰደ ነው የሚለው ሲሆን፤ ይህም ብዙ አፍሪካውያን እና ኤስያውያን ስደተኞች ወደዚህች በረሃማ ሀገር እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል፡፡
“አሁን ከሁሉም ሀገራት ስደተኞች ወደ አጋዴዝ እየመጡ ምክንያቱም የጥገኝነት ጥያቄ ለማቅረብ አሁን ቀለል ያለና አዲስ አሰራር ተጀምሯል ብለው ስላሰቡ ነው” ብለዋል የአጋዴዝ ከተማ ከንቲባ ሪሳ ፌልቶው፡፡
“በአሁኑ ሰዓት አጋዴዝ ውስጥ ቁጥራቸው ከጨመረው ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ከአፍጋኒስታን የመጡ ብዙ ሰዎች፣ ከሱዳን የመጡ ሰዎችና፣ ከቻድና የሌላ ሀገር ዜጎችም አንደሚገኙባቸው የአካባቢው ባለስልጣናት ነግረውኛል” ሲል በአካባቢው የሚኖር የዶቼቬሌ ጋዜጠኛው ቲላ አማዶው ለ InfoMigrants ተናግሯል፡፡
“በእርግጥ ሰዎች ከኒጀር እየተወሰዱ እንደሆነ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያነበቡ አንዳንድ ሰዎች እነሱም የዚህ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉ የመሰላቸው አሉ” ብለዋል የ UNHCR ባልደረባ የሆኑት ልዊስ ዶኖቫን፡፡
እነዚህ የውሸት ጭምጭምታዎች ምንጫቸው ከየት እንደሆን የተጠየቁት ዶኖቫን፤ መጀመርያ ላይ ትክክለኛ የነበረ መረጃ አንድያውን ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ እስኪዛባ ድረስ ከሰው ወደ ሰው ሲቀባበል እየተበረዘ እንደሚሄድ አብራርተዋል፡፡
በመሰረቱ እንዲህ ነው የሆነው፤ የአስቸኳይ ግዜ ስደተኞችን የማሸጋገር ዘዴ (ETM) ተብሎ የሚጠራ ስደተኞችን ከሊቢያ የማስወጣት መርሃግብር UNHCR እያከናወነ ነው፡፡ እነዚህ ስደተኞች በሊቢያ የእስር ማዕከላት መሄጃ አጥተው የነበሩና ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞች ናቸው፡፡ የዚህ መርሃግብር አንድ አካል በማድረግ ለግዜው ከሊቢያ ወደ ኒጀር ስደተኞችን በአየር ለማስወጣት እየሞከርን ነበር ብለዋል ዶንቫን፡፡
UNHCR ከህዳር ወር ጀምሮ እጅግ በጣም ተጋላጭ የሆኑ 1,084 ኤርትራውያን፣ ሶማልያውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሊቢያ አስወጥቷል፡፡
የአጋዴዝ ነዋሪዎችም በቅርቡ ከተማቸው ላይ እየጨመረ የመጣው የስደተኞች ቁጥር አሳስቧቸዋል፡፡ ኦማር ካታ የተባሉ የከተማዋ ኗሪ ለ InfoMigrants ሲናገሩ ወደ አጋዴዝ የሚመጡ ስደተኞች በድህነት ውስጥ ለምትኖረው ከተማ “ሸክም” ናቸው ብለዋል፡፡
“ሲጀምር ለአካባቢው ነዋሪዎች እንኳን እንደ ሆስፒታሎች እና መፀዳጃ ማዕከላት የመሳሰሉ በቂ መሰረተ ልማቶች የሉም፡፡ ሲጀምር በቂ መንግስታዊ አገልግሎቶች የሉም፡፡ እና እነዚህን ሁሉ ስደተኞች ማስተናገድ የሚችል መሰረተ ልማት የሚኖር ይመስላችኋል?” ብለዋል ካታ፡፡
“ዓለምአቀፉ የስደት ጉዳዮች ድርጅት (IOM) ቃልአቀባይ የሆኑት ሊዮናርድ ዶይል እንዲህ ሲሉ ጨምረዋል “ወደ ኒጀር እየመጡ ያሉት ሰዎች አብዛኞቹ ኢኮኖሚያዊ ስደተኞች ናቸው፡፡ የጥገኝት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ጥገኝነት የማግኘት ተስፋ የላቸውም፡፡”