የ 16 ስደተኞች ሬሳ በሊቢያ-ግብፅ ድንበር ላይ ተገኘ
(Photo-ፎቶ: የቀይ ጨረቃ ማህበር ሰራተኞች ባለፈው ሓምሌ ወር በሊቢያ ምስራቃዊ በረሃ ላይ ከምትገኘው ቶብሩክ አጠገብ የስደተኞችን ሬሳ ሲያነሱ፡፡ የፎቶ ምንጭ: ቀይ ጨረቃ ማህበር)
በዚህ ወር መጀመርያ ላይ፤ የሊቢያ የፀጥታ ኃይሎች ሊቢያን ከግብፅ ጋር በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢያ የ 16 ስደተኞችን ሬሳ አግኝተዋል፡፡ የስደተኞቹ ሬሳ የተገኘው በባህር ጠረፍ አቅራቢያ ከምትገኘው የቶብሩክ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ 310 ኪሜ ራቅ ብሎ ነው፡፡
የሊቢያ ቀይ ጨረቃ ማህበር ቃል አቀባይ የሆኑት ፋጢማ አል-ኦባይዲ እንዳሉት ከስደተኞቹ 13ቱ ግብፃውያን ሲሆኑ ከሚንያ፣ አስዩት፣ ሶሃግ፣ ኢስማልያ፣ ፋዩም እና ዳካልያ ግዛቶች የመጡ ናቸው፡፡
ሬሳዎቹን አግኝተው ያነሱት የቀይ ጨረቃ ማህበር እና የሊቢያ ጦር አባላት የስደተኞቹ በድን አካል ከመገኘቱ በፊት ረዘም ላለ ግዜ መቆየቱን እርግጠኞች ሆነዋል፡፡ የስደተኞቹ መታወቂያ ወረቀት እና ፓስፖርቶች በፈራረሰው የስደተኞቹ በድን አካላት ላይ ተገኝተዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ተመሳሳይ ክስተቶች አጋጥመዋል፡፡ በሓምሌ ወር መጀመርያ ላይ፤ የእርዳታ ሰራተኞች ወደ ሊቢያ በህገወጥ መንገድ በእግራቸው ተጉዘው እንዲገቡ ከተደረጉ በኋላ የተገደሉ ወይም በመንገድ መሪዎቻቸው ከተተዉ በኋላ የሞቱ ስደተኞችን ሬሳ ከሊቢያ ምስራቃዊ በረሃ ላይ አንስተዋል፡፡ በዚህ ክስተት፤ በአጠቃላይ 48 ግብፃውያን እንደሞቱ የተገመተ ቢሆንም፤ አንዳንዶቹ ሬሳዎች እጅጉን ከመፈረረሳቸው የተነሳ የአብዛኞቹን ማንነት መለየት አልተቻለም፡፡
ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ብዙ ግዜ በፀጥታ ኃይሎች ላለመያዝ ሲሉ እንዲሁም ደግሞ በረሃው መሃል መኪናዎቻቸው በሚበላሹበት ወቅት ስደተኞችን ጥለዋቸው ይጠፋሉ፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ