የአፍሪካ ስደተኛ ህፃናት ይበልጥ ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው
አዲስ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት በመነሳት በሜዲትራንያን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ከሚሰደዱት ህፃናት እና አፍላ ወጣቶች ሶስት አራተኞቹ በዚህ ጉዞ ላይ በርካታ የብዝበዛ ዓይነቶች ይደርሱባቸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና ዓለምአቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (ኣይኦኤም) ያወጡት ይህ ሪፖርት 11,000 ህፃናት እና ወጣቶችን ጨምሮ 22,000 ስደተኞች ላይ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፡፡
ብቻቸውን የሚጓዙ ህፃናት እና አፍላ ወጣቶች፤ በተለይም ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያለቸውና ጉዟቸው ለረጅም ግዜ የሚቆይ ከሆነ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ብሏል ሪፖርቱ፡፡ ሜዲትራንያንን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ከሚሞክሩት በ 14 እና 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞች ሶስት አራተኞቹ ጥቃት እና ብዝበዛ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
“አሳዛኙ እውነት በአሁኑ ሰዓት ሜዲትራንያንን አቋርጠው የሚጓዙ ህፃናት ላይ ጥቃት ማድረስ፣ ማዘዋወር፣ መምታት እና ማግለል እንደ ተገቢ ተግባር እየተቆጠረ መምጣቱ ነው” ብለዋል የዩኒሴፍ የስደተኞች እና የአውሮፓ የስደተኞች ጫና የሚመለከቱ ጉዳዮች ልዩ አስተባባሪ የሆኑት አፍሻን ካሃን፤ በመግለጫው ላይ፡፡
በመካከለኛው የሜዲትራንያን ክፍል ጉዞ ያደረጉ አፍላ ስደተኞች 25 ዓመት እና ከዚያ በላይ እድሜ ካላቸው ግማሽ ያክል ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ ሁለት ሶስተኞቹ ከፈቃዳቸው ውጪ መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡ ከግማሽ በታች የሚሆኑት አፍላ ስደተኞች ደግሞ በግድ ስራ እንዲሰሩ መገደዳቸውን ገልፀዋል፡፡
“ልትሮጥ ብትሞክር፤ ይተኩሱብሃል፡፡ መስራት ብታቆም፤ ይማታሉ” ሲል አይማሞ የተባለ ከጋምቢያ ብቻውን የመጣው ታዳጊ ሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ “እንደ ባሮች ነበርን” ሲል ሊቢያ ውስጥ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተገዶ የጉልበት ስራ ሲሰራ የነበረው ታዳጊ ይናገራል፡፡
ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ከሚመጡት ይልቅ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡት ይበልጥ ለብዝበዛና ለህገወጥ ዝውውር የተጋለጡ ናቸው፡፡ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሙከራ ከሚያደርጉት የሰሃራ በታች አፍሪካውያን ህፃናት 83 በመቶ ያክሉ ለብዝበዛና ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ የተጋለጡ ናቸው፤ ከሌላ ቦታ ከሚመጡት ግማሽ ያክሎቹ ጋር ሲነፃፀሩ፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመርያ የታተመ ሌላ ሪፖርት ላይ ደግሞ፤ IOM ከ 2014 አንስቶ 23,000 ያክል የስደተኞች ሞት መመዝገቡን ተናግሯል፡፡ ብዙ ያልተመዘገቡ ሞቶች ስለሚያጋጥሙ፣ ሬሳዎችም ሳይገኙ ስለሚቀሩና ማንነታቸው ለመለየት አዳጋች የሚሆንባቸው ግዚያት ስላሉ ትክክለኛው ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ሊል ይችላል፡፡
“ እነሱ [ስደተኞቹ] ክብራቸውን፣ ጤናቸውን እና ሂወታቸውን ማጣት ግድ ሊላቸው እንደሚችል እያወቁ አደገኛውን ጉዞ ያደርጋሉ” ብለዋል የአይኦኤሙ ዩጄንዮ አምብሮሲ፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ