ተመድ በሊቢያ ታግተው የሚገኙ ስደተኞችን ወደ ኒጀር ሊያስወጣ ነው

የፎቶ ምንጭ: AFP. ከሊቢያ የተመለሱ የአይቮሪኮስት ስደተኞች በፈረንጆቹ ህዳር 20/2017 ላይ በአቢጃን አየር ማረፊያ እንደደረሱ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት (UNHCR) ታህሳስ 11 ላይ እንዳስታወቀው፤ ሊቢያ ውስጥ መሄጃ አጥተው የሚገኙ 1,300 ተጋላጭ ስደተኞችን ከሀገሪቱ ሊያስወጣ ነው፤ ይህን ለማድረግ ያበቃውም ሀገሪቱ ውስጥ ያለው አስቸጋሪ ሰብአዊ ቀውስ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

UNHCR እስከ ጥር 2018 መጨረሻ፤ ከ 700 እስከ 1,300 የሚደርሱ እጅጉን ለችግር የተጋለጡ ሰዎችን ከሊቢያ ወደ ኒጀር ለማስወጣት አቅዷል፤ ይህም ጠባቂ የሌላቸው ህፃናት፣ የትዳር አጋር የሌላቸው እንስት ወላጆች፣ ለአደጋ የተጋለጡ ሴቶችና አስቸጋሪ የጤና ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሰዎች አንዲሁም ደግሞ ሊቢያ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ የተሰቃዩና የተንገላቱ ሰዎችን የሚያጠቃልል ነው፡፡

የኒጀር መንግስት እነዚህን ተጎጂዎች በግዚያዊነት ለማስጠለል የተስማማ ሲሆን ቀጣይ የጉዳያቸው ሂደት እና የሚሄዱበት ግዜ ግን በሂደት የሚታይ ይሆናል፡፡

“እጅጉን ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞችን በተቻለ ፍጥነት ከሊቢያ ማስወጣት እንፈልጋለን” ብለዋል የ UNHCR ረዳት የእንክብካቤ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ተርክ፡፡

“ግልፅ እየሆኑ የመጡትን ሰብአዊ ፍላጎቶችንን እና ሊቢያ ውስጥ በሚገኙ የእስር ማእከላት ላይ ከግዜ ወደ ግዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የሚገኘውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት፤ UNHCR በሚቀጥሉት ሳምንታት እና ወራት ሂወት-አድን ስደተኞችን የማስወጣት ስራዎችን ለማከናወን ብንቃት እየሰራ ነው” ብለዋል ተርክ፡፡

የመጀመርያው 25 ኤርትራውያን፣ ኢትዮጵያውያን እና ሱዳናውያን ስደተኞችን ያካተተው ቡድን ህዳር ወር ላይ ከሊቢያ ወደ ኒጀር እንዲወጣ ተደርጓል፡፡