የአውሮፓ ህብረት ኮምሽን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተወሰነባቸው ስደተኞች በእስር እንዲቆዩ ጥሪ አቀረበ

TMP – 26/03/2017

የአውሮፓ ህብረት ኮምሽን የህብረቱ አባል መንግስታት የጥገኝነት ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኙና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተወሰነባቸዉ ስደተኞች በእስር እንዲያቆዩ ጠየቀ፡፡

የህብረቱ ስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ዲመትሪስ አቭራሞፐውለስ በፌብሩዋሪ 28 እንደተናገሩት የህብረቱ አባል መንግስታት በ18 ወራት ውስጥ የሚያቀርቡትን የጥገኝነት ጥያቄ ምንም አይነት አሳማኝ ጉዳይ ያላቀረቡ ስደተኞች ላለመመለስ ሲሉ እንዳይሰወሩ ሲባል በእስር እንዲቆዩ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

‹‹የተመላሾች መጠን መጨመር አለበት›› ያሉት ዲመትሪስ አቭራሞፐውለስ የህብረቱ አስገዳጅ ያልሆነ እቅድ ይፋ ሲያደርጉ ‹‹ቀዳሚ ዓለማችን ምንም አይነት ጥበቃ የማይገባቸውና አውሮፓ ውስጥ ለመቆየት ህጋዊ መብት ላያገኙ ህገወጥ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚያደርጉትን አደገኛ ጉዞ መቀነስ ነው›› ብለዋል፡፡

ዲመትሪስ አቭራሞፐውለስ ስደተኞቹ በእስር በሚቆዩበት ወቅት ‹‹በተሻለ ሁኔታና በክብር›› መያዝ አለባቸውም ብለዋል፡፡ የኮሚሽኑ ረቂቅ እቅድ ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞች ይግባኝ የሚጠይቁበት የአጭር ጊዜ ቀነ ገደብ እንዲሰጣቸዉም ግምት ውስጥ ያስገባ እና ህጻናት ስደተኞችም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመመለስ በእስር እንዲቆዩ ለአባል ሃገራቱ የሚፈቅድ ነው፡፡

የህብረቱ ኮሚሽን በፍቃደኝነት ከአዉሮፓ የሚመለሱ ስደተኞች ለማገዝ የሚያስችል እቅድም ለመተግበር እያሰበ ይገኛል ፡፡ እስካሁን ድረስ ከሊቢያ ለሚመለሱ ስደተኞች በዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት  (IOM) በኩል የሚያደርገውን ድጋፍ እንዳጠናከረውም ተገልል፡፡