በሊቢያ የባህር ክልል አቅራቢያ በሰጠመችው ጀልባ የተሳፈሩ ስደተኞች ደብዛ መጥፋቱ ተገለጸ
በሊቢያ የባህር ዳርቻ ትሪፖሊ አቅራቢያ ከ100 በላይ ስደተኞች የጫነች ከፕላስቲክ የተሰራች አነስተኛ ጀልባ በመስመጧ 15 ህጻናትና ሴቶች የሚገኙባቸው 97 ስደተኞች ደብዛ መጥፋቱ ተገለፀ፡፡
የሊቢያ የባህር ክልል ጥበቃ ቃለ አቀባይ ጀነራል ኣዩብ ቃሲም በምዕራብ ትራፖሊ ወጣ ብሎ በሚገኘው ጋርግረሽ የተባለ የከተማዋ ዳርቻ 23 ስደተኞችን ከጀልባዋ ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
አብዛኛው የጀልባዋ አካል መውደሙን የገለጹት ቃለ አቀባዩ በህይወት የተገኙት 23 ስደተኞች ተበጣጥሶ በተንሳፈፈው የጀልባዋ አካል ተንጠላጥለው በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለነበሩት ባለስልጣናት በጭንቀት አደጋ ውስጥ መሆናቸው የሚገልጽ የድረሱልን ጥሪ ካሰሙ በኃላ ነው፡፡
ከሞት የተረፉት ስደተኞች ጀልባዋ ስትነሳ 120 ስደተኞች ጭና እንደነበር የገለጹ ሲሆን እነዚህ በህይወት ያልተገኙት ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የተናገሩት ቃለ አቀባዩ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ሬሳቸውን ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡
ህገወጥ የሠው ንግድ አዘዋዋሪዎች በሚድትራንያን ባህር ስደተኞችን ለማጓጓዝ ብቃት የሌላቸው አነስተኛ ጀልባዎች መጠቀም እያዘወተሩ ነው፡፡ በ2016 ብቻ እንኳን ከሊቢያ ወደ ጣልያን በሚያሻገረው የሚድትራንያን ባህር የ5000 ስደተኞች መሞት በከፍተኛ ሪከርድ ተመዝግቧል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ