ኢጣልያ በአንድ ወር ውስጥ 1000 ስደተኞች አስወጣች

የኢጣልያ መንግስት በዚህ ዓመት ውስጥ ጥያቄአቸው ውድቅ የተደረገባቸው 6,242 ስደተኞች ያስወጣ ሲሆን ይህም በየወሩ 1000 ስደተኞችን ከሃገሩ ማስወጣቱን ያመለክታል፡፡

ይህ ባለፈው ዓመት ከነበረው የተመላሾች ቁጥር ሲነጻጸር በ24% መጨመሩን ያመለከተው መረጃው አብዛኞቹ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ከሰሜን አፍሪካ የመጡ ህገወጥ ስደተኞች ናቸው።

ኢጣልያ በአሁኑ ሰዓት ህጋዊ የጥገኝነት ጥያቄን የሚመለከት ሰነድ የሌላቸው ህገወጥ ስደተኞችን ለመለየት የሌሎች ሃገሮች ትብብር በመሻት ላይ እንደምትገኝ የገለጸው ዘገባው ይህም ስደተኞችን በአፋጣኝ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ በፊት በጥቅምት ወር በበርሊን ገበያ ላይ ከባድ ተሸከርካሪ በመንዳት 12 ሰዎችን የገደለው አኒስ አምሪ የተባለው ቱኒዚያ አሸባሪ ወደ ሃገሩ ለመመለስ የተደረገው ጥረት መደናቀፉ የሚታወቅ ሲሆን ቱኒዝያ አሸባሪውን የሃገሯ ዜጋ እንዳልሆነ በመግለጽ የጣልያን መንግስት ያቀረበውን አሸባሪውን የመመለስ ጥረት መሰናከሉ የሚታወቅ ነው፡፡

በ2016 ከሰሜን አፍሪካ ሃገራት ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ኢጣልያ 18,684 ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው መመለሷ የሚታወቅ ነው፡፡

በተጨማሪም የኢጣልያ መንግስት ብዛት ያላቸው ባለሙያ ሰራተኞችን በመቅጠር የጥገኝነት ጥያቄዎችን በአፋጣኝ በመርመር እስከ ሁለት ዓመት ይፈጅ የነበረውን ጉዳይ በ6 ወር ውስጥ ተጠናቆ መልስ እንዲያገኙ እያደረገ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ስደተኞችን ከጎስቆላ ኑሮ ለመታደግ በመላው ኢጣልያ እንዲበተኑ እየተደረገ ሲሆን ይህም ስደተኞች በቂ ስልጠናና የቋንቋ ትምህርት በማያገኙባቸው ትንንሽ ከተሞች መኖር ያጋጥማቸው ነበረው ችግር የሚያቃልል ነው ተብሏል፡፡