በቀድሞው አቴንስ አውሮፕላን ማረፊያ የመጠለያ ካምፕ ሰፍረው የነበሩ ስደተኞች እንዲለቁ ተደረገ
የግሪክ ፖሊስ ሃይል ከጥቅም ውጭ ከሆነው የቀድሞው አቴንስ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው ጊዚያዊ የመጠለያ ካምፕ ህንጻ ከሰፋሪዎች ነጻ እንዲሆን አደረገ፡፡
እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ከሆነ በቁጥር በርከት ያለ የፖሊስ ሃይል ወደ መጠለያ ካምፑ ከየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ስደተኞች ሲጠቀሙበት የነበረውን መዳረሻና የትራንስፖርት መሳፈሪያዎች ሳይቀር እንዲዘጋ አድርጓል፡፡
አንድ የሃገሪቱ ቃል አቀባይ ስደተኞች ከመጠለያ ካምፑ እንዲወጡ ሲደረግ ምንም አይነት ግጭት አልተከሰተም ብለዋል፡፡
ይህ እስከ 2001 ዓ.ም የአቴንስ አውሮፕላን ማረፊያ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ቦታ አብዛኛዎቹ አፍጋኒስታውያን የሆኑ 3,000 ስደተኞች መጠለያ ካምፕ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አብዛኛዎች በመጠለያ ካምፕ መኖር የጀመሩ ስደተኞች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ቢደረግም በመቶዎች የሚቆጠሩ ግን ድንኳን ተክለው በስፍራው እየኖሩ ነው፡፡ የሰብአዊ መብት ተሞጋቾች ጊዚያዊ የመጠለያ ካምፑ ለረጅም ጊዜ መኖር ምቹ ባለመሆኑ የሃገሪቱ መንግስት ሌላ አማራጭ ቦታ እንዲያዘጋጅ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡
ባለፉት 10 ቀናት በካምፑ የቆዩ ስደተኞች ከአቴንስ ውጭ በተቋቋመው ተዛውረው እንዲሰፍሩ ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን 90% በአዲሱ ካምፕ ለመስፈር ፍቃደኛ ሲሆኑ የቀሩት ግን ለመዛወር ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የግሪክ ፖሊስ ቀደም ሲል የስደተኞቹ ቤተሰብ ከአቴንስ ውጭ ደቡባዊ ምዕራብ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ቴቤስ እንደሚዛወሩ ያሳወቀ ሲሆን ጥቂቶቹ ግን ወደ አዲሱ ካምፕ ከመዛወራቸው በፊት ማንነታቸውን ለመለየት ወደ አቴንስ ፖሊስ የአልየንስ ዳሬክቶሬት እንደሚወሰዱ ገልጿል፡፡
ቱርክና እና የአውሮፓ ህብረት ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚያደርጉት ጉዞ ለማቆም የመሻገሪያ ድንበሮችን ለመዝጋት ባለፈው ዓመት ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ 60,000 በላይ ስደተኞች ወደ ግሪክ ገብተዋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ