የሚድትራንያን ባህር በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚጓዙ ስደተኞች መሞት ቁጥር እየጨመረ ነው
በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚድትራንያን ባህር ሲያቋርጡ የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩ የዓለም የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) ገለጸ፡፡
በዚህ አደገኛው የባህር ጉዞ አውሮፓ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቢቀንስም በጉዞ ላይ የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር ግን ጨምሯል ፡፡
ከድርጅቱ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ባለፈው ዓመት 2016 ብቻ በዚህ የባህር ጉዞ 2512 ሲሞቱ በያዝነው 2017 ባሉት 6 ወራት ብቻ ግን 1650 ስደተኞች በባህር ላይ ሞተዋል፡፡
እንደ የእርዳታ ድርጅቶች መረጃ ከሆነ የስደተኞች መሞት እየጨመረ ያለው ሊቢያ ውስጥ የሚገኙ ህገወጥ የሰው ንግድ አዘዋዋሪዎች በሚያቀርብዋቸው ደረጃቸው ያልጠበቁ ጀልባዎች አማካይነት ነው ፡፡
በቅርቡ ከአቅማቸው በላይ ብዛት ያላቸው ስደተኞች የጫኑ ሁለት ትናንሽ ጀልባዎች ውስጥ የ50 ስደተኞች ህይወት በሊቢያ የባህር ክልል መጥፋቱም ከስፍራው የተገኘ መረጃ ይገልጻል፡፡
የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ቃለ አቀባይ ሊዮናርድ ዶይል “የሟቾች ቁጥር መጨመር ጣራ ላይ ደርሷል፣ እነዚህ ሰዎች ስራና ገቢን በመሻት በነዚህ አነስተኛ ደህንነታቸው የማያረጋግጡ ጀልባዎች ለማቋረጥ ይገደዳሉ ራሳቸውን ለአደጋ በማጋለጥ መጨረሻቸው በአሳዛኝ ሁኔታ ይቋጫል፡” ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን (UNHCR) በቅርቡ በሚድትራንያን ባህር ያጋጠመውን ክስተት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከምዕራብና ምስራቅ አፍሪካ ወደ ሱዳን፣ ኒጀርና ሊቢያ የሚጎርፉ ስደተኞች ቁጥር እየናረ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑና የህገወጥ አዘዋዋሪዎች የጭካኔ ተግባርም በዚያው ልክ እያደገ መምጣቱን ገልጿል፡፡
ድርጅቱ በመግለጫው “ሊቢያ ውስጥ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ኢሰብአዊ ተግባርና ጭካኔ ስደተኞች ወደዚያች አገር ከመድረሳቸው በፊት በሚያቋርጡባቸው ሃገራት የተለየ መፍትሄ ለማምጣት ሁላችንም ከተለመደው ውጭ አዲስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡” ብሏል፡፡
ብዙ ስደተኞች ወደ ሊቢያ የባህር ክልል ከመድረሳቸው በፊት በሰሃራ ምድረበዳ የሚሞቱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ