ስለ ህገወጥ ስደት አደጋዎች ግንዛቤ ማሳደግ በኢትዮጵያ
የማህበረሰብ ውይይት መርሃግብር በቡታጅራ፤ ኢትዮጵያ። ፎቶ: አይኦኤም 2017
የህገወጥ ስደት አደጋዎችን በተመለከተ ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ማህበረሰብ-መሰረት-ያደረገ የሙከራ እንቅስቃሴ፤ በሶስት ዓመታት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ግማሽ ሚልዮን ሰዎችን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ አወያይቷል።
የማህበረሰብ ውይይት መርሃግብሩ አገልግሎት በዓለምአቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) እና በኢትዮጵያ መንግስት በ 2014 የተጀመረ ሲሆን፤ በህገወጥ ስደት ተጠቂ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች ላይ አነጣጥሮ የሚሰራና በርዕሰ ጉዳዩ ዙርያ ያሉትን የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚጋፈጥ ነው፡፡
አይኦኤም እንደሚለው፤ መርሃግብሩ አነጣጥሮ በሚሰራባቸው አካባቢዎች ላይ ትምህርት የማቋረጥ መጠን ለመቀነስ ማስቻሉን እና የማህበረሰቡ አባላት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ማየት በመጀመራቸው ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች እና አስተላላፊዎች ላይ የሚወሰደው የህግ እርምጃ ጨምሯል።
ውጭ አገር ይገኛል በተባለ ሃሰተኛ የስራ ቃል ተታልለው፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አብዛኛውን ግዜ ገንዘባዊ፣ አካላዊ፣ ፆታዊና ስነልቦናዊ ጥቃት የሚያስከትልባቸውን ጉዞ ለማድረግ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን ይጠቀማሉ።
ችግሩን ለመግታት፤ ኢትዮጵያ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል አጠቃላይ ድንጋጌ አስተላልፋለች። ባለፈው ዓመት ስራ ላይ የዋለው ህጉ፤ ህገወጥ የሰው ዝውውር እና ስደተኞችን ማስተላለፍ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ላይ የሚጣለውን ቅጣት ያከበደ ሲሆን በይበልጥ በመከላከል ስራ ላይ እና ድንበር-ዘለል ትብብር ላይ የሚያተኩር ነው።
ፅሑፉን ያካፍሉ