የ 24 ስደተኞች ሬሳ በትሪፖሊ አቅራቢያ በባህር ዳርቻ ተገኘ

-A baby carrier-

ሜዲትራንያንን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሙከራ በማድረግ ላይ ሳሉ የሞቱ 24 ስደተኞች ሬሳ በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ የባህር ዳርቻ ላይ ከባህሩ ተገፍቶ ወጥቶ ተገኝቷል።

ይህን አስደንጋጭ ክስተት ያስታወቀው የሊቢያው ቀይ ጨረቃ ማህበር ነው። “ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ስለሁኔታው ጥቆማ ከደረሰን በኋላ ሬሳዎችን መሰብሰብ ጀመርን” ብለዋል የቀይ ጨረቃ ማህበር አባል የሆኑት ሆሳም ናስር።

“የሰበሰብናቸው ሬሳዎች አጠቃላይ ብዛት 24 ነው፤ ከቦታው አቀማመጥ አስቸጋሪነት የተነሳ ከባድ ነበር” ሲሉ አክለዋል።

አብዛኛውን ግዜ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ የሚያሸጋግሩ ደካማ ጀልባዎች ባንድ ግዜ ከ 100 ሰዎች በላይ ስለሚጭኑ ቁጥሩ ከዚህ በላይ ከፍ እንደሚል ተጠብቋል።

በተመሳሳይ ቀን፤ ከምዕራባዊቷ የሳብራታ ከተማ 13 ኪሎሜትሮች ገደማ ራቅ ብሎ፤ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች 19 ሴቶች እና አራት ህፃናት የሚገኙባቸውን 147 ሰዎች ታድገዋል።

የባህር ጠረፍ ጥበቃው ቃል አቀባይ ጄኔራል አዩብ ቃሲም እንዳሉት ከአቅሟ በላይ በታጨቀችው ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት 147 ስደተኞች አብዛኞቹ ከካሜሩን፣ ሱዳን፣ ሴኔጋልና ማሊ የመጡ ናቸው።

ዓለምአቀፍ የስደተኞች ድርጅት እንደሚያመለክተው፤ በ 2017 እስካሁን ድረስ 72,000 ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ኢጣልያ ደርሰዋል፤ እንዲሁም ደግሞ ጉዞውን በማድረግ ላይ ሳሉ 2,000 ሰዎች ባህር ላይ ሞተዋል።