የአውሮፓ ህብረት ሚኒስትሮች የስደተኞችን ፍሰት ለመቀነስ በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ተወያዩ

የአውሮፓ ህብረት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገሮች ተነስተው በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚጓዙ ስደተኞችን ፍሰት ለመቀነስ በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ለመወያየት በቅርቡ በኢስቶንያ ተሰብስበዋል።

ሚኒስትሮቹ የሊቢያን የባህር ጠረፎች ጥበቃና ሂወት የመታደግ አቅም የሚጠናከርበትን እንዲሁም የሊቢያ ደቡባዊ ድንበሮች ይበልጥ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተዋል።

የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት መግለጫቸው፤ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ዜጎቻቸውን ለመቀበል በማይፈቅዱ ስደተኞች የመጡባቸው ሀገራት ላይ የቪዛ ገደብ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ገልፀዋል።

የኢጣልያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ፤ በሊቢያ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ውሃዎች ላይ የስደተኞችን ሂወት ለመታደግ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚሰሯቸው ተግባራት ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ባለስልጣናት ጋር በቅርበት ሊከወኑ ይገባል ብለዋል።

“እነዚህ ሲቪላዊ ተግባራት ናቸውና ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች እና የምርመራ ስራዎችን በሚመለከት ከፍትህ አካላት እና ከፖሊስ ጋር በጥምረት ሊሰሩ በሚያስፈልጋቸው ልክ መቀናጀት ይገባቸዋል” ብለዋል።

የኢስቶኒያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አንድርያ አንቨልት ዓለምአቀፋዊ ጥበቃ ሊደረግላቸው መብት የሌላቸው ስደተኞች በፍጥነትና ብቃት በተሞላው መንገድ ወደየሀገሮቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ አፅንዖት ሰጥተውበታል። “ህጋዊ ስደት እንደ አንድ አማራጭ የሚወሰድ ቢሆንም፤ ነገር ግን ህገወጥ ስደትና ኢኮኖሚያዊ ስደት ግን ሊቆሙ ይገባቸዋል” ብለዋል አንቨልት።

ሚኒስትሮቹ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃን ማጠናከር፣ ጥገኝነት ጠይቀው ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው መመለስ እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት ስራ ለመፈለግ ወደ አውሮፓ እንዲሰደዱ የሚያደርጋቸውን ድህነት ለመቅረፍ የሚከናወኑ የልማት ጥረቶችን በገንዘብ መደገፍ በሚሉት ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።

ሮም ውስጥ በተደረገ ሌላ ጉባኤ፤ ኒጀር፣ ቻድ እና ሱዳን ስደተኞች ወደ ሊቢያ እንዳይደርሱ ለማድረግ በይበልጥ ድንበሮቻቸውን እንዲጠብቁ የሚያግዝ የ 10 ሚልዮን ዩሮ ድጋፍ እንዲሁም ደግሞ በበጎ ፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች የሚውል ሌላ ተጨማሪ የ 18 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የኢጣሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንጀሊኖ አልፋኖ አስታውቀዋል።

ወደ ሊቢያ የሚሄዱ ስደተኞችን ማስቆም አለብን፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ በስተደቡብ የሚገኙትን ሀገራት መደገፍ ይኖርብናል” ብለዋል አልፋኖ።