የአውሮፓ ህብረት ለኢጣልያ የሚሆን የስደተኞች ዕቅድ አቀረበ

ከሊቢያ በመነሳት ሜዲትራንያንን አቋርጠው በሀገሪቷ የባህር ዳርቻዎች ላይ የሚደርሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ጉዳይ ለመጨረስ እንዲያስችላት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለኢጣልያ 35 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብቷል።

በኢጣልያ የጥገኝነት ጥያቄ የሚስተናገድበትን እና ስደተኞች ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ስርዓት የበለጠ ብቁ ለማድረግ የሚያግዝ መሪ ዕቅድም ይፋ ተደርጓል። እነዚህ አዲስ እርምጃዎች ወደ ኢጣልያ ከሚደርሱት አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት ብዙ የኢኮኖሚ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱን ስራ ያፋጥናሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጎባቸዋል። ኢጣልያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማቆያ ስፍራ አስራ የምታቆይበትን የግዜ ገደብ ለመጨመር የቀረቡ ዕቅዶችም አሉ።

በተጨማሪም፤ ኢጣሊያ ከዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ ስደተኞች የተቀናጀ በበጎ ፈቃድ የመመለስ እና ከቤተሰብ ጋር የመቀላቀል አሰራሩን እንድትጠቀምበት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኢጣሊያን እያበረታታ ነው።

ስደተኞች ከሊቢያ የሚደረገውን አደገኛ የጀልባ ላይ ጉዞ እንዳያደርጉ ለመግታት፤ የሊቢያን የባህር ጠረፍ ጥበቃ በስልጠናና መሳርያዎች ለማጠናከር መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚገባ ዕቅዱ አስታውቋል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽኑ ዕቅድ በኢጣሊያና በሌሎች የሜዲትራንያን ሂወት አድን ድርጅቶች መካከል የተሻለ ትብብር እንዲኖር ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ ቱኒዝያ፣ ግብፅ እና አልጄርያ የአውሮፓ ህብረት ህገወጥ ስደትን ለመግታት የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀላቀሉ ያበረታታል።