አንድ ታጣቂ የሊቢያ ቡድን፤ ስደተኞች ወደ አውሮፓ እንዳይሄዱ እያስቆመ ነው
“በቀድሞ የወሮበሎች አለቃ” የሚመራ አንድ ይፋዊ ያልሆነ ታጣቂ ቡድን ከሊቢያዋ ከተማ ሳብራታህ ተነስተው ወደ አውሮፓ ለመሄድ የሚሞክሩ ስደተኞች የጫኑ ጀልባዎችን እያስቆመ ነው፡፡
ከመዲናዋ ትሪፖሊ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ 70 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሳብራታህ የሚገኙ ምንጮች እንዳሉት፤ በባህር ጠረፍ አካባቢ በምትገኘው ይህች ከተማ ታጣቂ ቡድኑ ስደተኞች በጀልባ ወደ ኢጣሊያ የሚያደርጉትን ጉዞ ለመግታት የባህር ዳርቻ ላይ ሆኖ ነው ስራውን የሚያከናውነው፡፡
ምንጮቹ እንደሚሉት፤ ቡድኑ በርካታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች፣ ፖሊሶችና ታዋቂ መኮንኖች የሚገኙበት ሲሆን ቀደም ሲል የወሮበሎች አለቃ በነበረ ግለሰብ የተጀመረውን ጠንካራ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ነው፡፡
ቡድኑ፤ ከጉዞ እንዲመለሱ የተደረጉ እና ከህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ የተወሰዱ ስደተኞች የሚታጎሩበት የእስር ማዕከል ያስተዳድራልም ተብሏል፡፡
ለባህር ጉዞ አመቺ በመሆኑ ምክንያት፤ ባለፉት ዓመታት፤ ሓምሌ እና ነሓሴ ወራት ላይ ከሊቢያ ወደ ኢጣሊያ የሚጓዙ ጀልባዎች ይበዙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን፤ 2016 ላይ ከነበረው ተመሳሳይ ግዜ ጋር ሲነፃፀር፤ በዚህ ዓመት የሓምሌ ወር ከሊቢያ ተነስተው ኢጣሊያ የደረሱ ስደተኞች ቁጥር ከግማሽ በታች ቀንሷል፡፡ የነሓሴ ወር ቁጥር ደግሞ ከዚህም ያነሰ ነው፡፡
“ባህሩ ባለፈው ሳምንት ልክ እንደ ሃይቅ ፀጥ ያለ ነበረ፤ ነገር ግን ጀልባዎቹ ጥቂት ነበሩ” ብለዋል ማይግራንት ኦፍሾር ኤይድ ስቴሽን (MOAS) የተባለውን የእርዳታ ድርጅት ካቋቋሙት መካከል አንዱ የሆኑት ክሪስ ካትራምቦን፡፡
የዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት ፍላቪዮ ዲ ጂያኮሞ እንደሚሉት፤ ባለፈው ሳምንት ሜዲትራንያን ላይ ሂወታቸው መታደግ የተቻለ ስደተኞች እንዳረጋገጡት ሳብራታህ ላይ የነበሩት ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል፡፡
“ከሳብራታህ ተነስቶ ጉዞ ማድረግ ከባድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ጀልባዎች ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት የሚያስቆሙ ሰዎች አሉ፤ ወደ ባህሩ ከሄዱም ወድያውኑ እንዲመለሱ ይደረጋሉ” ብለዋል ዲ ጂያኮሞ፡፡ አንዳንድ ስደተኞችም ወደ ሳብራታህ ከመድረሳቸው በፊት ተመልሰዋል ሲሉም አክለዋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ